በአማራ ክልል ለ2 ሚሊዮን 982 ሺህ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት መሰጠቱ ተገለጸ።

55

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለ2 ሚሊዮን 982 ሺህ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መስጠት መቻሉን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ገለጸ። በኢኒስቲትዩቱ የበሽታዎችና ጤና ኹኔታዎች ቅኝትና ምላሽ ቡድን አሥተባባሪ ፅጌረዳ አምሳሉ ፣ በክልሉ ከአምስት ዓመት በታች ለሚገኙ ሕጻናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ክትባቱ ከመስከረም 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ከአራት ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን አስረድተዋል። እስካሁን በተከናወነ እንቅስቃሴም 2 ሚሊዮን 982 ሺህ ሕጻናትን መከተብ እንደተቻለ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅትም የክትባት ዘመቻው መቀጠሉን አመልክተው፣ እስካሁን ልጆቻቸውን ያላስከተቡ ወላጆችም ከወዲሁ ፈጥነው ማስከተብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የፖሊዮ (የልጅነት ልምሻ) በተበከለ ምግብና ውኃ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ፣ ለዘላቂ የአካል ጉዳትና ሞት የሚዳርግ እንደኾነ ጠቁመዋል። የክትባቱ ዘመቻ ዓላማ የልጅነት ልምሻን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን የገለጹት አስተባባሪዋ፤ ለክትባት ዘመቻው መሳካት ሁሉም አካል ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን እንዴት እንጠቀም?
Next article“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላት ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው” የአፍሪካ ኅብረት