
አዲስ አበባ: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲሰ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አሥተዳደር በመሬት አሥተዳደር ዙሪያ አገልግሎትን ለማሻሻል እየሠራቸው ያሉ ሥራዎችን ጉብኝተዋል። በመድረኩ የአዲሰ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያለአግባብ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለማሻሻል የሚያስችል ዲጅታላይዜሽን እና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዋች እየተሠሩ ነው ብለዋል
ከንቲባ አዳነች ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ የሥራ ቦታዎችን ለተገልጋይ ምቹ የማድረግ ሥራም እየተሠራ እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት። ለሕዝቡ ቃል በተገባው መሠረት ለማገልገል ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሠራባቸው ሥራዎች መካከል አንዱ የመሬት አሥተዳደር ነው ብለዋል፡፡ ከንቲባዋ በተቋማት ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን የዲጅታል አገልግሎትን ለባለጉዳዮች ለመስጠት እየተሠራ ያለውን ሥራ በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።
የመሬት ሕጎችን ሙሉ በሙሉ የማሻሻል እና የመሠብሠብ ሥራ እና ሪፎርሙን መሸከም የሚችል አደረጃጀት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የቴክኖሎጅ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም የሲስተም ልማት ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። የመረጃ አያያዝ እና አሥተዳደር ሥርዓቱን የማሻሻል ሥራም እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው በቴክኖሎጅ የታገዘ ቅንጅታዊ አሠራር እና ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር መቻላቸውንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አሥተዳደር ላይ የታየው የመሬት አያያዝ ሥርዓት ሌሎች ከተሞችም ልምድ ሊወስዱበት የሚችሉበት ነው ብለዋል፡፡ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የዲጅታል አገልግሎት አሰጣጡ ጊዜ እና ጉልበትን የቆጠበ እንዲሁም የተገልጋዮችን እንግልት የሚቀርፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከተሞች ያላቸውን አቅም በመጠቀም ለነዋሪዎች ምቹ የኾነ የሥራ አካባቢን መፍጠር እና አሠራሮችን ዲጂታላይዝ ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!