ሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊ እና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአሥተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እንደሚያስፈልግ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

32

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በጄኔቫ እየተካሄደ ባለው 149ኛ ኢንተር ፓርላሜንት ኅብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ አፈ ጉባኤ አገኘው በመድረኩ በዓለም ላይ እየታየ ያለውን ፈጣን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዕድገት በአግባቡ ማሥተዳደር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊ እና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአሥተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ በመኾኑ ፓርላማው በጉዳዩ ላይ ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ፓርላማዎች አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ለማሥተዳደር ሕጋዊ ደንብ በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ኀላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ችግሮችን ለመፍታት እና የቴክኖሎጅ መሻሻል የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሳደግ በመንግሥታት መካከል የጋራ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል። ሳይንስ እና ቴክኖሎጅን ለተሻለ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመጠቀም ብሎም ሥነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመተግበር የኅብረቱ ቻርተር አዎንታዊ ሚና እንደሚጫዎትም ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅ እና ብሔራዊ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፖሊሲ ማዕቀፍን ጨምሮ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅን ለአዎንታዊ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመጠቀም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች እንደተጠበቁ ኾነው በቂ የዲጅታል መሠረተ ልማት ግንባታ አለመኖር እና የአቅም ክፍተት አሁንም እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዲጅታል ሽግግርን ለማቀላጠፍ የተሻለ ትብብር እና አጋርነት እንዲኖርም ጠይቀዋል።

የዘላቂ ልማት ግቦች እና አጀንዳ 2030 በመላው ዓለም እንዲሳካ ኅብረቱ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የዘወትር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አፈ ጉባኤ አገኘሁ መግለጻቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጋራ እና በትብበር የምንፈልጋትን አፍሪካ እንገንባ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next article“የአዲሰ አበባ ከተማ የዲጅታል አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዮችን እንግልት የሚቀርፍ ነው” የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ