“በጋራ እና በትብበር የምንፈልጋትን አፍሪካ እንገንባ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

47

አዲስ አበባ: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‘አፍሪካ በጠንካራ አንድነት ለሁለንታዊ ፀጥታ እና ሰላም’ በሚል መልዕክት የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ዓድዋ ሙዚየም እየተካሄደ ነው። ጉባኤውን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “እዚህ የተሰባሰብነው ችግራችንን ልናወራ ብቻ ሳይኾን ተሰባስበን በመነጋገር መፍትሔ ልናመጣ ጭምር ነው” ብለዋል።

“የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ” የሚለው መልዕክት በሁሉም ዘርፍ ተግባራዊ መኾን ይኖርበታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፀጥታ እና ከትብበር አንፃር መታየት ያለባቸው ጉዳዮች በአግባቡ መታየት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ የአፍሪካን ፍላጎት እና ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጋራ ቆምን ማስከበር ይኖርብናል፤ ይህ ደግሞ ሉዓላዊነታችንን፣ ክብራችንን እና አስፈላጊ ነገሮች እንዲሟሉ ያደርጋልም ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋራ ኾነንም የምንፈልጋትን እና የምንመኛትን አፍሪካ አንገባ ሲሉም ለአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጥሪ አቅርበዋል። የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ ሙሐመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የፀጥታ ጠበቃ ናት፤ በአንድነት ኾነን የአፍሪካን ጥንካሬ ለማምጣት በተካሄዱ ሥራዎች ሁሉ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል፡፡

ይህ ኮንፈረንስ መሰባሰብ ብቻ ሳይኾን አፍሪካን አንድ እንዳትኾን ወደ ኋላ የሚጎትቷትን ለማስቆም ለሚደረገው ጥረት ጠቃሚ ነውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አፍሪካ ያሉባትን ችግሮች ተቋቁማ ጠንካራ እና ለልማቷ የምትሠራ አሕጉር እንድትኾን ይህ ኮንፈረንስ እና ስብስብ ትልቅ ሚና አለው። ለአፍሪካ ሰላም እና ፀጥታ ጠቃሚ ነው ብቻ ብለን የምናልፈው ሳይኾን የሚያስፈልገንም የምንጥርለትም ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።

በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች እና ፀረ ሽብር ተጠሪ ቦባቱንዴ ሃዌሚ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላም በርካታ ሰራዊት በማዋጣት ለአፍሪካ ሰላም መስዋዕትነት የምትከፍል ናትም ብለዋል። ቀጣናዊ ተቋማት በአፍሪካ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት መጠናከር ይገባዋልም ነው ያሉት።
በአሕጉሪቱ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መሠረታቸውን አውቀን በመፍታት ለአሕጉሪቱ ሰላም እና መሻሻል መሥራት ይገባል ብለዋል።

አንድ ስንኾን የመታገል እና የማሸነፍ አቅማችንን አይተናል፡፡ በሶማሌ እና በዲሞክራቲክ ሪ ብሊክ ኮንጎ የሰራናቸው ሥራዎች ለዚህ ትልቁ ማሳያ ነው ሲሉም አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ክልሉ በተወሳሰበ የጤና ችግር ውስጥ ነው ያለው” በላይ በዛብህ
Next articleሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ እና ፈጠራን ለበለጠ ሰላማዊ እና ዘላቂ አኗኗር ለመጠቀም የሚስችል የአሥተዳደር ማዕቀፍ ማበጀት እንደሚያስፈልግ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡