“ክልሉ በተወሳሰበ የጤና ችግር ውስጥ ነው ያለው” በላይ በዛብህ

30

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጅ ፎረም እየተካሄደ ነው። ፎረሙን ያዘጋጀው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው።

በስትራቴጅክ ፎረሙ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ክልሉ ላለፉት አምስት እና ከዚያ በላይ ዓመታት ከፍተኛ የሰብዓዊ እና የቁሳዊ ቀውስ እየደረሰበት ነው ብለዋል። በጦርነቶች እና ግጭቶች ምክንያት በደረሰው ችግር እና በሌሎች ችግሮች ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በተፈጠረው ውስጣዊ ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ሰበዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እየደረሰ መኾኑን ነው የተናገሩት። ረጅም የኾነ የውስጥ ግጭት፣ የሰዎች መፈናቀል፣ ወረርሽኞች እና ሌሎች ችግሮች እንዳሉ ነው የተናገሩት። ከፍተኛ የኾነ የዓለም አቀፍ ድጋፍን የሚጠይቅ ምላሽ የመስጠት ፍላጎት እንዳለም አስረድተዋል። የጤና ድርጅቶች እና የጤና ባለሙያዎች ሰበዓዊ መብት የኾነውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉም አስገንዝበዋል። በክልሉ ያሉት ኹኔታዎች ክልሉ በተወሳሰበ የጤና ችግሮች ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል ነው ያሉት።

የመንግሥት መዋቅሩ ከሚሠራው በተጨማሪ መንግሥታዊ ተቋማት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል። እንዲህ አይነት ከፍተኛ የቅንጅት አሠራር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ ያለው ሥራ ከችግሩ ስፋት አንጻር በቂ አለመኾኑንም ተናግረዋል። ጤና ሰበዓዊ መብት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ማንኛውም ሰው የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አለው፣ የጤና ተቋማትም ከየትኛውም ጥቃት መጠበቅ አለባቸው ብለዋል። በጤና ጉዳት የሚደርስበትን ማኅበረሰብ ለመታደግ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾን ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በወባ በሽታ ታሞ ሕክምና መስጫ ላይ እየተገኘ መኾኑንም አስታውቀዋል። ይሄም እስካሁን ከታየው ሁሉ ከፍ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት። የሚቀጥሉት ወራት ደግሞ የወባ በሽታ ሊስፋፋ እንደሚችል ነው የገለጹት። ሊደርስ የሚችለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ለወባ በሽታ እና ሌሎች ሕክምናዎች ምላሽ ለመስጠት የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋማት በነጻነት እንዲሠሩ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በግጭትም ኾኖ የጤና አገልግሎት መሰጠት ግድ መኾኑን ተናግረዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት ፎረም እያደረገው ላለው በጎ ተግባር አመሥግነዋል።ዓለም አቀፍ ተቋማት በአማራ ክልል በቂ ድጋፍ እያደረጉ አለመኾናቸውንም አንስተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤና አገልግሎቶች ያለ ምንም መስተጓጎል እና ክልከላ ለክልሉ ሕዝብ ተደራሸ በማድረግ ሰብዓዊ ቀውስን መቀነስ እንደሚገባ ተጠቆመ።
Next article“በጋራ እና በትብበር የምንፈልጋትን አፍሪካ እንገንባ” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ