የጤና አገልግሎቶች ያለ ምንም መስተጓጎል እና ክልከላ ለክልሉ ሕዝብ ተደራሸ በማድረግ ሰብዓዊ ቀውስን መቀነስ እንደሚገባ ተጠቆመ።

30

ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የጤና አገልግሎቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፎችን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጅ ፎረም እየተካሄደ ነው። ፎረሙን ያዘጋጀው በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ነው። በስትራቴጅክ ፎረሙ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተገኘተዋል። በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ዘርፎች ችግሮች እየተከሰቱ መኾኑ ተመላክቷል።

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ጸሐፊ ታፈረ መላኩ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ባለፉት ዓመታት በክልሉ የሚገኙ ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች በማስተባበር በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል። በሰሜኑ ጦርነት የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለክልሉ አርሶ አደሮች የሙያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች የመስኖ እርሻ እንዲሠሩ መደረጉንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ትራክተሮችን በመግዛት የመስኖ እርሻ ውስጥ እንዲገቡ እና ተጨማሪ ምርት እንዲያመርቱ ተደርጓል ነው ያሉት። ፎረሙ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ስትራቴጅ ዶክመንቶችን እና ጥናታዊ ጽሑፎችን በምሁራን እንዲዘጋጁ በማድረግ ለክልሉ መንግሥት ማቅረቡን አስታውቀዋል።

በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው ሁሉን አቀፍ ቀውስ እንደተከሰተ ፎረሙ ሰነድ በማዘጋጀት ቀውሱ ሳይባባስ መፍትሔ እንዲሰጠው ምክረ ሃሳቦችን የያዘ ጥናታዊ ጽሑፍ ለክልሉ መንግሥት ማቅረቡንም ገልጸዋል። ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት ለብዙዎች በማመቻቸት የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራታቸውንም አመላክተዋል።

የክልሉ ሕዝብ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ችግር ላይ በወደቀበት ጊዜ ሁሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተናጠል እና በጋራ አያሌ የሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል። ፎረሙ ባለፉት ዓመታት ለችግር ደራሽ እንደነበርም ገልጸዋል። የችግሩን ስፋት በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይኾኑ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በማስረዳት ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በተፈጠረው ግንዛቤ መሠረት ከክልሉ ውጭ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ በጦርነት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ድጋፎችን ማድረጋቸውን ነው የገለጹት። መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ከፎረሙ እና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። ፎረሙ ለክልሉ ማኅበራዊ ዕድገት የተለየ ትኩረት በመስጠት የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ለተቋማት ማስረከቡንም ገልጸዋል።

በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ዝቅተኛ ውጤት መመዝገቡን ተከትሎ መላው የትምህርት ማኅበረሰብ በቁጭት ወደ ንቅናቄ እንዲገባ ፎረሙ ትልቅ ድርሻ መወጣቱንም ተናግረዋል። በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በክልሉ የደረሰውን ጉዳት እንዲጠና እና በመጽሐፍ መልኩ እንዲታተም ማድረጉንም ገልጸዋል። ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የደረሱ ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመጽሐፍ መልኩ እንዲታተሙ አድርጓል ነው ያሉት።

የዛሬው ስትራቴጅ ሰነድም ዋና ዓላማ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ያለ ምንም መስተጓጎል እና ክልከላ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለክልሉ ሕዝብ ተዳራሸ በማድረግ ሰብዓዊ ቀውስን መቀነስ እና የተጨነቁ ሰዎችን መታደግ ነው ብለዋል። ስትራቴጅ ሰነዱ አንደኛውን ወገን ለይቶ አይወነጅልም፣ የጥፋተኝነት ደረጃም አያወጣም፣ መሠረታዊ መነሻውም ይሄ አይደለም፣ ፍርዱን ለሕዝብ መተው ተገቢ እና ትክክል ኾኖ አግኝተነዋል ነው ያሉት።

የሰብዓዊ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት መሠረታዊ ዓላማ አንጻር ጉዳዩን ቢያጠኑት የተሻለ እንደሚኮንም አመላክተዋል። በክልሉ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ልብ ሰባሪ እንደኾነም አንስተዋል። በሐዘን ድባብ ከመቆዘም እናቶችን፣ ሕጻናትን እና እየተጎዱ ያሉ ንጹሐንን መታደግ እና የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይደርስ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ሰብዓዊ ድጋፍ ለሁሉም ተደራሽ እንዲኾን እና የተጨነቁ ሰዎችን ለመታደግ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የታጠቁ ኀይሎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን በተለይም የጄኔቫ ኮንቬክሽኖችን እንዲያከብሩ እና መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲኾኑ ቀና ትብብር እንዲያደርጉ ማስተማር፣ መቀስቀስ እና መሞገት ይገባል ነው ያሉት።

የግጭቱ ዋና ተዋንያኖች ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲያከብሩ እና ለስትራቴጅ ትግበራ ሙሉ ትብብር እንዲያደርጉ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በክልሉ የተከሰተውን ሁሉን አቀፍ ቀውስ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሽብርተኝነትን መዋጋትን ዓላማው ያደረገ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
Next article“ክልሉ በተወሳሰበ የጤና ችግር ውስጥ ነው ያለው” በላይ በዛብህ