
ባሕር ዳር: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአሕጉሪቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፤ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ ለቀጣይ ሶስት ቀናት ይቆያል። በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በጉባዔው አሕጉራዊ የጸጥታ ማዕቀፎችን ማጠናከር እና የሀገራትን ወታደራዊ የትብብር አቅም ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለደኅንነት ስጋቶች ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋልም ተብሏል።
በተጨማሪም አሕጉራዊ ወታደራዊ ግብዓቶችንና ትጥቆችን በራስ አቅም ማሟላት በሚያስችሉ ጉዳዮች እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሚና ላይ በመምከር ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ አፍሪካ ለሚያጋጥማት ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅምን በማሳደግ በወታደራዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል።
የጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች እና ወታደራዊ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃና የልማት ሥራ እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!