
ደባርቅ: ጥቅምት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ጎን ለጎን ተማሪዎችን የመመዝገብ እና ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ አስታውቋል። በዞኑ መመዝገብ ከነበረባቸው 336 ሺህ 502 ተማሪዎች መካከል 124 ሺህ 812 ተማሪዎች ተመዝግበዋል። የዕቅዱን 44 በመቶ መሸፈን መቻሉንም የሰሜን ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ባየ መርሻ ገልጸዋል።
ተወካይ ኀላፊው በዞኑ ከሚገኙ 565 ትምህርት ቤቶች መካከል 192 ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ ጀምረዋል ብለዋል። የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፈረደ ይትባረክ እንደገለጹት በደባርቅ ከተማ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት ከደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በደባርቅ ከተማ የነባሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች የመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ትምህርት በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውንም ነው ለአሚኮ የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!