
ገንዳ ውኃ: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እና ሰላም እንዲሰፍን ለሚደረገው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ የምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር መንግሥት ሠራተኞች ገልጸዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የመጀመሪያው የመንግሥት ሥራ ኾኖ ሊቀጥል የሚገባው የጠራ ሰላም እና ፍትሐዊ የኾነ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ነው ብለዋል፡፡
ችግር እና መከራን እስከዛሬ ድረስ በጀርባችን አዝለነው የቆየነው ይበቃናል፤ አሁን ላይ ሰላም እና ልማት ነው የምንፈልገው፤ ሲሉ ታሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የሰላም ማስከበሩን ጉዳይ አጠናክሮ ከቀጠለ ከመንግሥት ጎን በመኾን ለሰላም ዘብ እንደሚቆሙ የውይይቱ ተሳታፊዎች አሣሥበዋል።
የፀጥታ መዋቅሩ ላስገኘው አንፃራዊ ሰላም አመስግነው፣ ሰላም በሕይዎት ለመኖራችን ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ነውም ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ካልተማሩ፣ የመንግሥት ሠራተኛው ካልሰራ፣ አልሚ ባለሃብቶች ካላለሙ እና አርሶ አደሩ ካላረሰ ሀገር ወደ ፊት ልትቀጥልም ኾነ ታሪኳ ሊወሳ አይችልም ሲሉ የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አብዱልከሪም ሙሐመድ አሳውቀዋል። “አማራ ክልል በራሱ ልጆች ስቃዩ እና መከራው በዝቶበታል፤ እናም ክልሉ እንደሌሎች ክልሎች እንዳይለማ እና እንዳያድግ እንቅፋቱ ብዙ ነው“ ሲሉ የዞኑ የብልጽግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እያሱ ይላቅ አሳስበዋል።
“ሁላቹሁም ሰላምን በመሻት ከመንግሥት ጎን በመኾን የዞናቹሁን ሰላም ማረጋገጥ እና የክልላችንን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ይገባል“ ያሉት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ እና ምክትል አሥተዳዳሪው አንዳርጌ ጌጡ ናቸው። እናቶች በወሊድ ምክንያት፣ ሕፃናት እየታገቱ እና አቅመ ደካማ አረጋዊያኖች ሰላም እያጡ፣ በመንገድ መዘጋት ምክንያት ሕይዎታቸው የሚያልፉ ዜጎች እየተበራከቱ ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አድማ ብተና አዛዥ ኮሚሽነር አበበ ውቤ ናቸው፡፡
“ነፍጥ ያረፈበት ምድር ድህነት፣ የሰው ሃብት ቅነሳ እና በኢኮኖሚ መድቀቅን ካልኾነ በስተቀር ሀገርን የሚያሳድግበት ኾነ የሚገነባበት አንድም ኹነት የለውም“ ያሉት ደግም የሰሜን ምዕራብ እዝ የ504ኛ ክፍለ ጦር አሥተባባሪ ብርጋዴር ጄነራል አብደላ ሙሐመድ ናቸው ። የመንግሥት ሠራተኛው ከአሉባልታ እና የፕሮፓጋንዳ ወሬ ራሱን ጠብቆ ሰላምን በመሻት እና ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሽ ሊወጣ ይገባዋል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ኤርቄሎ ዱካቶም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!