በግልጽ ችሎት በመዳኘት ፍትሕን የማስፈን ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

51

ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 የሥራ ዘመን የዳኝነት አገልግሎትን ጀምሯል። የዳኝነት አገልግሎቱ ምቹ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለበት እንዲኾን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተተግብረዋል። ግልጽ ችሎቶችም ሥራ ጀምረዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ ወርቁ ያዜ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎቶች በግልጽ እንዲዳኙ ለማድረግ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። ባለ ቀጠሮዎችንም በግልጽ ችሎት መዳኘት መጀመሩንም ተናግረዋል። ዳኞች ሥራቸውን በግልጽ ችሎት እንዲያስችሉ እና በልዩ ኹኔታ ካልተከለከለ በስተቀር የወንጀልም የፍትሐ ብሔርም ከሳሽ እና ተከሳሽ ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት ነው መታየት ያለበት። ይህም ጉዳዩን ሕዝብ እየተከታተለው መዳኘቱ ከብልሹ አሠራር እና ከአሉባልታ ማዳን ያስችላል ነው ያሉት።

ዳኝነትን በግልጽ ማስቻሉ ምስክር በሚሰማበት ጊዜ ሕዝብ ስለሚከታተለው በሐሰት መመስከርን እንደሚቀንስ፣ ዳኞች የበለጠ ተጠንቅቀው እንዲዳኙ እንደሚያደርግ እንዲሁም ፍትሕ በደላሎች ይጓደላል የሚለውን የኅብረተሰቡ ስጋት እንደሚቀረፍም ነው አቶ ወርቁ የገለጹት። የዳኝነት ሥርዓቱን ምቹ በማድረግ እና በዲጂታላይዜሽን በማገዝ የተቀላጠፈ ፍትሕ ለመሥጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው። በመጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም ተመሳሳይ ማሻሻያዎችን በመተግበር የዳኝነት አገልግሎቱን ግልጽ፣ ፈጣን እና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ቢንያም ዮሐንስ በበኩላቸው የ2017 የሥራ ዘመን የዳኝነት አገልግሎት በግልጽ ችሎት መጀመሩ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። በግልጽነት እና በተጠያቂነት መርህ መፈጸም ለሁሉም ባለጉዳይ እና ለሚዲያ ግልጽ ማድረግ ማለት ነው ብለዋል።

ግልጽ ችሎት ማለት የአዳራሽ ችሎት ብቻ ሳይኾን ሥራዎችን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ዜጎች የፍርድ ቤቶችን ሥራ በግልጽ እንዲከታተሉ የማስቻል ሂደትንም እንደሚጨምር ገልጸዋል። ለዚህም በሦስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚሳካ የዲጂታላይዜሽን ሥራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል። ከወረዳ ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ የዳኝነት ሂደቶችን በኔትወርክ በማገናኘት ተገልጋዮች ባሉበት ወረዳ ኾነው ጉዳያቸውን መከታተል የሚችሉበት አሠራር ለመፍጠርም በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በኢ-ፋይሊንግ መዝገቦችን ከወረቀት ነጻ በማድረግ በኮምፒዩተር እና መሰል ኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች አያያዝ ዘዴ በመጠቀም መሥራትም በቅርቡ እንደሚተገበር ተናግረዋል። ይህም ዜጎች ቤታቸው ኾነው የዳኝነት ሥርዓቱን እና ሂደቱን መከታተል የሚችሉበት ነው ብለዋል። የተከራካሪ ወገኖችን እና የፍርድ ቤቶችን ሃብት እና ጉልበት በመቆጠብ እንዲሁም በፍጥነት እና በግልጸኝነት በመሥራት የዳኝነት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ ቢንያም የገለጹት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰንደቅ ዓላማን ክብር ለትውልድ ማሻገር ይገባል” የወልድያ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አለማየሁ ነጋ
Next article149ኛው ዓለም አቀፉ ፓርላማ በተላያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡