“በልጆችሽ የተከበርሽ፤ ጠላቶችሽ የማይደፍሩሽ”

27

ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በሰማይ ላይ ያበራሽ፣ በየአፍላጋቱ ላይ የተኳልሽ፣ በተራራዎች አናት ላይ ከፍ ከፍ ያልሽ፤ በትውልድ ልቡና ላይ የተጻፍሽ፣ የአበው ቃል ኪዳን ያለብሽ፣ የእመው አደራ ያረፈብሽ፣ የከበረ ማሕተም የታተመብሽ፣ ተስፋ ላጡት ተስፋ የኾንሽ፣ በነጻነት የኖርሽ፣ የነጻነት ምልክትም የተባልሽ፣ ልጆችሽ አብዝተው የሚወዱሽ፣ ጠላቶችሽ የሚንቀጠቀጡልሽ፣ አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለብሽ፣ በደም ማሕተም ጸንተሸ ክብር እንሰጥሻለን፣ ለክብርሽ እጅ እንነሳለን፣ ለግርማሽ እንጎናበሳለን፡፡

ኀያላኑ የሚጠብቁሽ፣ የረቀቀ ምስጢር የታተመብሽ፣ የማይዝል ኀይል ያለሽ፣ የማይጠፋ ብርሃን የሚበራብሽ፣ የማያረጅ የማይጠወልግ ግርማን የተቸርሽ፣ ጽናትን የታደልሽ፣ በጠላቶችሽ ሰማይ ሥር በክብር የተውለበለብሽ፣ በክብርሽ የመጡትን ሁሉ ድል የነሳሽ፣ ለክብርሽ እንዲያጎነብሱ ያስደፋሽ የማትደፈሪው ሠንደቅ ልጆችሽ አብዝተው ይወዱሻል፤ ሕይወታቸውን ሁሉ ይሰጡሻል፡፡

ነጻነት የሌላቸው ነጻነትን ያገኙብሽ፣ በባርነት የኖሩ ጌትነትን የተቀበሉብሽ፣ ጨለማ የወረሳቸው ብርሃንን ያዩብሽ፣ የመውጫ ምልክት ያደረጉሽ፣ የመከራ ዘመን መሻገሪያ የኾንሽ፣ ልጆችሽ በአንድነት የተሠባሠቡብሽ፣ በአንቺ ምክንያት መለያየትን ያራቁብሽ፣ አንቺን አስቀድመው ድልን የተቀዳጁብሽ፣ ነጻነትን ከዓለት አጠንክረው ያኖሩብሽ፣ ሉዓላዊነትን ያላስነኩብሽ፣ የመተሳሰሪያቸው ረቂቅ ገመድ ያደረጉሽ፤ ስለ ፍቅርሽ መስዋዕት የከፈሉልሽ፣ ደም እና አጥንታቸውን የገበሩልሽ፣ ሕይዎታቸውንም አሳልፈው የሰጡሽ፣ ወደ መቃብርም ሲወርዱ እንዳትለያቸው ከፈናቸው ያደረጉሽ፣ በመቃብራቸውም ራስጌ ላይ የሰቀሉሽ ሰንደቅ ልጆችሽ ይመኩብሻል፣ በክብርሽ ክብራቸውን ይገልጡብሻል፡፡

ትውልድ ሁሉ በፍቅርሽ ገመድ የሚተሳሰርብሽ ታላቋ ሰንደቅ ክብር ይገባሻልና ክብር ይሰጥሻል፡፡ ልጆችሽ በዓለም አደባባይ ድልን በተቀዳጁ ጊዜ አንቺን ለብሰው በደስታ ያለቀሱልሽ፣ የፍቅርሽን ነገር በእንባ እና በለቅሶ የሚገልጹሽ፣ ከሁሉም ልቀሽ እንድትውለበለቢ የሚታገሉልሽ፣ በላባቸው ድልን ተቀዳጅተው ከፍ አድርገው የሚያውለበልቡሽ፣ በዓለሙ ፊት ከፍ ከፍ የሚያደርጉሽ፣ ፍቅርን እና ድል አድራጊነትን የሚገልጹልሽ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩዋ ሰንደቅ ከሁሉም ትልቂያለሽ፤ ከሁሉም ትበልጭያለሽ፣ ከሁሉም ትቀድሚያለሽ፤ በዓለሙ ሁሉ በድል ብቻ ትታወሺያለሽ፡፡ ድል ለአንቺ የተሰጠ ነውና፡፡

ኢትዮጵያውያን ያጌጡብሻል፣ ከዓለሙ ሁሉ ይለዩብሻል፣ ቃል ኪዳንን ይቀበሉብሻል፣ ይከበሩብሻል፣ ደስታ እና ፍቅርን ያገኙብሻል፡፡ ጥቁሮች ሁሉ የባርነት ልብሳቸውን አውልቀው አንችን በክብር ለብሰውሻል፣ የክብር መጎናጸፊያ አድርገውሻል፤ የነጻነት ማሕተማችን፣ የመከራ ዘመን መውጫ መንገዳችን እያሉ አወድሰውሻል የተዋብሽው፣ የተከበርሽው፣ በከፍታም የኖርሽው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሰንደቅ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሰንደቅ ዓላማ ያላት ሀገር መኾኗን ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን አንድ ስታደርጋቸው፣ ስታሠባሥባቸው፣ በጀግንነትም ስታጸናቸው የኖረችው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሰንደቅ ዓላማ ናት፡፡ ለዘመናት በነጻነት እንዲኖሩ ያደረጋቸው በሰንደቅ ዓላማቸው ሥር በአንድነት ተሠብሥበው በጀግንነት ስለታገሉ እና በጀግንነት ጠላቶቻቸውን ድል ስለመቱ ነው፡፡

ይህች ሰንደቅ ዓላማ ከጥንት ዘመን ጀምራ የኖረች፤ ኩራት እና ክብር ያላበሰች፣ በማንም ያልተደፈረች፣ የሉዓላዊነት እና የነጻነት መገለጫ ናት፡፡ “ ጀግኖች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ክብር እና ዝና አስጠብቀዋል፡፡ ስለ እርሷም አያሌ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በምድሯ ብቻ ሳይኾን ከመድሯም ተሻግረው ከፍ አድርገዋታል፡፡ በሦስተኛው ቃኘው ሻለቃ ወደ ኮሪያ የዘመቱ የኢትዮጵያ አርበኛ ግርማይ በየነ በአንድ ወቅት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያን ጀግኖች አርበኞች ለኮሪያ መኖር ባበረከቱት አስተዋጽኦ ከሁሉም ሀገራት በተለየ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብላ ለ15 ደቂቃ በኮሪያ ምድር እየዞረች እንደተውለበለበች ነግረውን ነበር፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አንዳቸውም በጠላት እጅ ሳይወድቁ ሁሉም ሀገራቸው እና ንጉሳቸው የሰጧቸውን አደራ ተውጥተዋል፣ ከሁሉም ሀገራት የላቀ ጀብዱ እና ጀግንነት ፈጽመዋልና ነው፤ ከሁሉም ሀገራት ተለይታ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ኾነች፡፡ በዙሪያዋ ያሉ የሌሎች ሀገራት ወታደሮችም ለኢትዮጵያ ክብር ሰጧት፡፡ አርበኛው ግርማይም በዚያ ወቅት የተሰማኝ ኩራት እና ደስታ እጥፍ ድርብ ነበር በማለት ያስታውሱታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በኮሪያ ምድር ሰንደቃቸውን አስቀድመው እናት ሀገራቸው የሰጠቻቸውን አደራ ሲወጡ፣ የእነርሱንም እገዛ ለሚፈልጉ ኮሪያውያን ሲዋደቁ አስደናቂ ነገርን አድርገዋል፤ ከሌሎች ሀገራት ወታደሮች የተለየ ገድል ፈጽመዋልና “እኛ በሠራነው ጠመንጃ ይህን ሁሉ ምርኮኛ ስንስጥ እነሱ ግን አንድም ሳይሰጡ የጠላት ምርኮኛ ይሠበሥባሉ። ጀግንነታቸው ልክ የለውም” ብሎ አንድ አሜሪካዊ የጦር አዛዥ ኢትዮጵያውያንን ሲያደንቅ መስማታቸውንም አርበኛ ግርማይ ነግረውን ነበር፡፡

ሰንደቅ የሀገር ምልክት፣ የታላቅነት፣ የሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡ ግርማዊ ቀደማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያንን ወራሪ ድል አድርገው ሲገቡ በቤተ መንግሥታቸው በመጀመሪያው ያደረጉት ነገር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው መስቀል ነበር፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ ስትሰቀልም ጥሩምባው እና እምቢልታው እየተነፋ፣ ነጋሪቱ እየተጎሰመ፣ እልልታው ከዳር እስከ ዳር እየተስተጋባ፣ ከበሮው እየተመታ፣ በሕዝብ እየታጀበች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በንጉሠ ነገሥቱ እጅ ተሰቀለች ብለው ጽፈዋል በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው፡፡ ሰንደቅ ዓላማዋ በንጉሡ እጅ በተሰቀለችበት ጊዜ 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሶ እንደ ነበርም የታሪክ ጸሐፊው ያስታውሳሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን ሰንደቃቸውን አብዝተው ይወዷታል፤ ያከብሯታልና ዛሬም ስለ እርሷ ይዋደቁላታል፡፡ ለክብሯም ይቆሙላታል፡፡ ሁልጊዜም በልባቸው ብራና ላይ ጽፈው ያኖሯታል፡፡ ከቀናት መካከል አንዷን ቀን መርጠው ደግሞ በዓል ያከብሩላታል፡፡ ይህች የተመረጠችው ቀንም ዛሬ ናት፡፡ ዛሬ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ብሔራዊ አንድነትን ትፈጥራለች፣ ሉዓላዊነትን ታስከብራለች፣ ኢትዮጵያን ከፍ ታደርጋለችና፡፡

ይህችን ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተከብራ የኖረች ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን በጽናት ያኖሯታል፡፡ አንድነታቸውን ይጠብቁባታል፤ በአንድነትም ሀገራቸውን ያስጠብቁባታል፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀዩዋ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን የኩራት፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት ምልክት ናት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብዙ ሁነን እንደ አንድ በመቆም ለኢትዮጵያ ከፍታ የምንነሳበት ጊዜ ነው” ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ
Next articleየረጅም ጊዜ ጊዜያዊ (ኮንትራት) ቅጥር ማስታወቂያ