በኮንትሮባንድ ንግድ ሀገር ልታጣ የነበረውን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

56

አዲስ አበባ: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀሙን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት በጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ ከ87 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ አቅዶ ከ88 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሠብ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም የዕቅዱን 100 ነጥብ 86 በመቶ ማሳካት ማስቻሉን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በመግለጫቸው አንስተዋል። ኮሚሽነሩ በኮንትሮባንድ ገቢ ወጭን ከመከላከል እና ከሕገወጥ የንግድ ቁጥጥር ሥራዎች አኳያም በሩብ ዓመቱ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶችን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ብቻ በኮንትሮባንድ ንግድ ሀገር ልታጣ የነበረውን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ጠቁመዋል። ተቋሙ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት አንፃርም 34 ነጥብ 20 ቢሊዮን ብር ከተጠቃሚዎች መገኘቱ ነው የገለጸው። ተቋሙን በልህቀት በመገንባት ወደ ስኬት ለማምጣት ጠንካራ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዚህ ሩብ ዓመት ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። አንዳንድ ክፍተቶችን አርሞ በሩብ ዓመቱ የተገኘውን ስኬት ለማስቀጠል ኮሚሽኑ በትጋት እንደሚሠራም በመግለጫው ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመጨረሻው ምሽጋችን…
Next article“ብዙ ሁነን እንደ አንድ በመቆም ለኢትዮጵያ ከፍታ የምንነሳበት ጊዜ ነው” ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ