
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካ በየትኛውም የሥራ መስክ ከተሠማሩ ዜጎቿ ይልቅ ለወታደሮቿ የምትከፍለው ደመወዝ ላቅ ይላል፡፡ ብዙ ሀገሮችም ዜጎቻቸው ሀገራቸውን ወታደር ኾነው እንዲያገለግሉ ግዳጅ ያስቀምጣሉ፡፡ በኛ ሀገር ለወታደሮች እና ሌሎች የፀጥታ አካላት የምንከፍላቸው አድናቆትን እንጅ ሕይዎታቸውን ለሚገብሩበት ሙያቸው የሚመጥን ምንዳ ነው ማለት ይቸግራል፡፡
አንደኛው ሲክብሽ አንዱ ያፈርስሻል አንዱ ሲያሳድግሽ አንዱ ይዘርፍሻል እንዳለ ከያኒው ስንኞች እዚህ ቦታ ላይ ያመጣናቸው ለሀገራችን የመጨረሻው ምሽግ ስለኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጥቂት ማለት ፈልገን ነው፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንደ ስሙ ሁሉ ሀገርን ከሚደርስባት እና ከደረሰባት ችግር መከላከል ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከራሱ ሕዝብ እና ሀገር አልፎ የሌሎች ሀገራትን ሰላም በማስከበር የሚታወቅ ነው፡፡ ኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሌሎችንም ሀገራት እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሌሎች ሀገራትን ሰላም እንዲያስከብር አመኔታ የተጣለበትም ኾነ ብቃቱ የሚመዘነው በተግባር ባሳያቸው የአገልጋይነት ሥነ ልቦናው ነው፡፡ በታማኝነቱ ነው፤ በሌሎችም ልኬታዎች ከፍ ብሎ በመቀመጡ ነው፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከምንም በላይ የሚያስቀድመው ሀገሩን እና ሰንደቅ ዓላማውን ነው፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ለመጡበት ጠላቶች ምትክ የሌላት ሕይዎቱን ጭምር ይሰጣል፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ልዩ ብቃትን ከሚጠይቀው ወታደራዊ ሥልጠና እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጅዎችን መጠቀም ድረስ ባሉ ፈተናዎች ውስጥ በእሳት ተፈትኖ የሚያልፍ ወርቅ መኾኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡
ውኃ ጥም፣ ብርድ፣ ሀሩር፣ ዝናብ፣ ውሽንፍር፣ ተራራ መውጣት፣ ቁልቁለት መውረድ፣ መራብ፣ እና ሌሎችም ፈተናዎች ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሠርክ ተግባሩ እንጅ ፈተናዎቹ አይደሉም፡፡
እስኪ ከራሴ ልጀምር ወቀሳ
ምን ሠራሁ ላገሬ ልጠየቅ ልነሳ
እስኪ ሁላችን ያብከንክን ይቆጨን
ከራስ ስደት ሌላ ምን ታሪክ አቆየን
ገና ሀገር ማለት ትርጉሙ አልገባንም
የባንዲራ ኩራት ውሉ አልተረዳንም
እንደ ታሪካችን እንደ ጥንት ቀደምቱ
ላንድነት እንጣር ወገኖቼ በርቱ፡፡
ዕውነቱ ከያኒው እንዳለው ነው፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ለሀገራችን ምን ሠራላት ብለን ከመጠየቃችን በፊት “እኔ ለሀገሬ ምን ሠራሁላት” ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ገና ሀገር ማለት ትርጉሙ አልገባንም … እንዳለው ከያኒው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ለሀገራችን ህልውና መከበር ያለው ፋይዳ ያልገባን ገና ብዙ ሰዎች አለን፡፡
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስለ ሀገር ደኅንነት ተብለው ከመንግሥት የሚሰጡትን ግዳጆች ሁሉ በብቃት በመወጣት ይታወቃል፡፡ በሀገር ውስጥ የሚታዩ የሰላም መደፍረሶችንም የሕይዎት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ለሰላም ዋጋ ከፋይ ኾኖ ዘልቋል፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ የሚዘነጋ ኢትዮጵያዊ አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ወረራው ወደ አማራ ክልል በዘለቀበት ወቅትም ወራሪውን ኀይል አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ከፊት ኾኖ የተሰለፈው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንደ ነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
አርሶ አደሮችን በማሳ ተገኝቶ የሚያግዝ፣ ልዩ ልዩ የሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያደርገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለዚህ ሁሉ በጎ ተግባሩ የሚከፈለው ምንዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ መከላከያ ሠራዊትን የአንድ ሰው፣ ብሔር፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ወይም ሌላ ጠባቂ አድርጎ መሳል ጉልህ ስህተት ነው፡፡ እኛ በእጅጉ የምንሳሳላትን ሕይዎታችንን እነሱ ለሀገራቸው ለመገበር ወጥቶ አደር (ወታደር) የኾኑ አካላትን በሞቀ ቤት ውስጥ ኾኖ መውቀስ ፍጹም ስህተት ይኾናል፡፡
ሀገራችን ከየአቅጣጫው ለሚሰነዘሩባት ዛቻ እና ማስፈራሪያዎች መከላከያ ይኾነናል ብለን የምንጠብቀው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንን ነው፡፡ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስንል፣ በሰማይ፣ በምድር፣ በውኃ እና በሌሎችም ኹኔታዎች ሀገራችንን ከጠላት የሚጠብቅልንን ኀይል ማለታችን ነው፡፡
ወንዝ እያለሽ አልለማሽም
ልጅ እያለሽ አልተጦርሽም
ውለታሽስ ይኼው ነወይ
ሀገሬ ሰው አጣሽ ወይ
ሀገሬ አሳቢ አጣሽ ወይ
ሀገሬ ልጅ አጣሽ ወይ?
ይኼን የሚጠይቁን የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ናቸው ብለን እናስብና ቀና ቀናውን እንመልስላቸው፡፡ እነሱ በሙያቸው እና በሕይዎታቸው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየጣሩ ነው፤ እኛስ? ሁላችንም በተሰማራንበት ሙያ ለሀገራችን ምን አበረከትንላት? አበርክቷችን እንደ ሠራዊቱ እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት እንዲኾንስ አሥበናል ወይ? ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፈን የሀገርን ሥንክ ሳር ለማስወገድስ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን? ራሳችንን እንጠይቅ፤ ለራሳችንም እንመልስ፡፡
በዚህም ተባለ በዚያ ግን የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር የመጨረሻው ምሽግ መኾኑ መዘንጋት የለበትም፤ ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ የውጭ ጠላት ባሰጋቸው ቁጥርም ተስፋቸው እና መተማመኛቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊታቸው ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!