
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)“ስንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ17ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።
በአማራ ክልልም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በልዩ ልዩ ሥርዓቶች ተከብሯል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “ሰንደቅ ዓላማችን ኅብረብሔራዊ አንድነታችን አጣምሮ የያዘ የማንነታችን የጋራ ምልክት ነው” ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ የሀገሪቱ መለያ፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት መገለጫ መኾኑንም አንስተዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሲከበር እንደ ሌሎች ሀገራት የነጻነት ቀንን በማሰብ ሳይኾን የቆዬ ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የዘለቀች ሀገር መኾኗን በማሰብ መኾኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለፓን አፍሪካኒዝም ትግል ማቀጣጠያ ኾኖ አገልግሏል ነው ያሉት። በዚህ ዘመንም የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ለመላቀቅ በታገሉ የአፍሪካ ሕዝቦች ውስጥ የነጻነት ምልክት እና ኩራት ኾኖ የሚታይ ነው ብለዋል።
አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራትም የሰንደቅ ዓላማቸው መነሻ አድርገው መጠቀማቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይም የሰንደቅ ዓላማውን ክብር ላለማስደፈር ብዙዎች መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ይህንን የሉዓላዊነት መገለጫ የኾነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ኀይሎችን መታገል የዚህ ትውልድ ኀላፊነት መኾኑንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!