
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአጣዬ ከተማ እና አካባቢው በተደጋጋሚ ሲከሰቱ የነበሩ የሰላም እጦቶች ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ሲያሳድሩ ቆይተዋል፡፡ የሰላም እጦቱ ጫና ካሳደረባቸው ተቋማት መካከል የትምህርት ዘርፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሰላም እጦቱ ከፈተናቸው ተማሪዎች መካከል በአጣዬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው አሸናፊ አልታዬ አንዱ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት ያጋጠመው የሰላም እጦት በመማር ማስተማሩ ሥራ ላይ ችግር መፍጠሩን ተማሪዎች ይናገራሉ። ከመስከረም 22 እስከ መስከረም 24/2017 ዓ.ም ድረስ የአጣዬ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በኤፍራታና ግድም ወረዳ የሚገኙ ሦስት ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን የ2ኛ ዙር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን አስፈትነዋል።
ተማሪ አሸናፊ አልታዬ ያጋጠመውን ፈተና ተቋቁሞ 515 ውጤት በማስመዝገብ ፈተናዎችን ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳያ ኾኗል። በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ትምህርቱን ቢማር ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይችል እንደ ነበር የሚናገረው ተማሪ አሸናፊ የሰላም እጦቱ እያሳደረው ያለው ተፅዕኖ ከባድ በመኾኑ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብሏል፡፡
በተለይም ጦርነቱ በተማሪዎች ላይ ሥነ-ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር በመኾኑ ችግሩን ለማስተካከል ሰፊ ሥራዎች ሊሠራ እንደሚገባም አስገንዝቧል። ተማሪ አሸናፊ አልታዬ በኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ ተምሮ በተሻለ ውጤት በመመረቅ ሀገሩን እና ወገኑን ለማገልገል ህልም እንደሰነቀም ለአሚኮ ገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!