
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችን እና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በአማራ ክልል የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለ17ኛ ጊዜ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንደሚከበር በተሻሻለው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 ተደንግጓል፡፡ ዛሬ ረፋድ ላይም በአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ተከብሯል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያውያን የነጻነታችን ምልክት፣ የአርበኝነት ምሰሶ፣ የብዝኃነታችን ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው ብለዋል፡፡ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓሉን ከማክበር ባለፈ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር እና ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ይህንን የነጻነት ምልክት የኾነ አርማ የሚገባውን ክብር መስጠት እና ማክበር የዚህ ትውልድ ኀላፈነት እና ግዴታ ሊኾን ይገባልም ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!