
ባሕር ዳር: ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ጀግኖች ከራሳቸው በላይ ሀገራቸውን ይወዳሉ፣ ልበ ሙሉዎች ሁልጊዜም ታላቅነትን ያስባሉ፣ የሀገርን ክብር ይጠብቃሉ፣ የሀገርን ከፍታ ያስጠብቃሉ፣ ታማኞች እስከ መቃብር ድረስ ለቃል ኪዳናቸው ይጸናሉ፤ ቆራጦች ከነፍሳቸው በላይ ሀገራቸውን ይወዳሉ፣ ከሁሉም በፊት ሀገራቸውን ያስቀድማሉ፤ ስለ ሠንደቅ ዓላማዋ ክብር ይዋደቃሉ፣ ሥለ ነጻነቷ የመከራ ፅዋን ይጎነጫሉ፡፡ መከራ በበዛበት ጎዳና ይመላለሳሉ፣ ስለ ሀገራቸው ሁሉንም ይችላሉ፡፡
እልፍ ጠላቶች ተነሱባት ልጆቿ እልፎቹን አሸነፏቸው፣ እልፍ ባንዳዎች ወጡባት እልፎቹን ጣሏቸው፣ አያሌ ቅኝ ገዢዎች አንዣበቡባት አንዳቸውንም ሳያስቅሩ ድል መቷቸው፣ በአንደበታቸው ኢትዮጵያን ይጠራሉ፣ በደማቸው ቀለም የኢትዮጵያን ስም ጎላ አድርገው ይጻፋሉ፣ በክንዳቸው ብርታት ሀገርን ያቆማሉ፡፡ እነርሱ አልፈው ሀገርን ያኖራሉ፤ እነርሱ ወድቀው ሀገርን ያጸናሉ፡፡ እነርሱ ተርበው ሀገሬውን ያጠግባሉ፣ እነርሱ ድንጋይ ተንተርሰው እያደሩ ሀገሬውን በምቾት ያኖራሉ፣ ድንበሩ እንዳይሰበር፣ ክብሩ እንዳይፈር በጀግንነት ይጠብቃሉ፡፡ እፍኝ የማትሞላ የኮዳ ውኃ ጠጥተው፣ ከጉሮሮ የማትወርድ ኮቸሮ በልተው ስለ ሀገር በጀግንነት ይቆማሉ፡፡
ዘመን ከተቆጠረ፣ ታሪክ ከተነገረ ጀምሮ ኢትዮጵያን ድል ያደረጋት፣ በምድሯ ላይ የሰለጠነባት፣ ልጆቿንም በቅኝ ግዛት ቀንበር ያደረገባት አልተገኘም፡፡ እርሷን የሚያሸንፋት፣ እርሷን ድል የሚያደርጋት አይገኝምና፡፡ እርሷ ለድል የተፈጠረች፣ ለአሸናፊነት የተመረጠች ናትና፡፡ ኃያላን ነን ያሉ ተነስተውበታል፣ እርሷ ግን ሁሉንም ቀጥታቸዋለች፡፡
ከኃያላን በላይ የረቀቀች ኃያል መኾኗን አሳይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ማሕፀን ሁልጊዜም ጀግና ይወልዳል፤ የኢትዮጵያ ምድር ሁልጊዜም ጀግና ያሳድጋል፡፡ ጀግናው የሚያድግበት፣ አንድነት ያላበት ሀገር ደግሞ ጠላት አይደፍረውም፣ ነፋስ አያወዛውዘውም፣ እንደ ዓለት ይጠነክራል፣ እንደ ተራራ ይገዝፋል እንጂ፡፡
ኢትዮጵያን ተዋት አትችሏትም፣ ልጆቿ ከእሳት የላቁ ናቸውና ይለበልበችኋል፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ትጠፋላችሁ፣ ስማችሁን ከታሪክ መዝገብ ላይ ትሰርዛላችሁ፣ በዓለሙ ፊት ትዋረዳላችሁ፣ የማትነካዋን ነክታችሁ አንገታችሁን ትደፋለችሁ፤ ከአሁን ቀደም የነኳት አልቀዋል፤ ተዋርደዋል፣ አንገታቸውን ለዘላለም ቀና ላያደርጉ ደፍተዋል፤ የዓለሙ ሁሉ መሳቂያ መሳለቂያ ኾነዋልና፡፡
ኢትዮጵያን አትንኳት ልጆቿ ብርቱዎች ናቸው ማንም የማይገፋቸው፣ ኢትዮጵያን ተዋት ልጆቿ ከዓለት የጠነከሩ ማንም የማይነቀንቃቸው ናቸውና ትጠፋላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ ድል ከላይ የተሰጣት፣ ማንም ምንም ሊያደርጋት የማይችላት፣ ጥንታዊት እና ቀዳማዊት ሀገር ናትና፡፡ ዶናልድ ሌቪን በጻፉትና ሚሊዮን ነቅንቅ በተረጎሙት ትልቋ ኢትዮጵያ የብዙ ነገዶች ማኅበረሰብ በተሰኘው መጽሐፍ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ታላቅ ሀገር የነበረች፣ ዝነኛ እና ኃይለኛ የኾነች፣ ሃብታም እና በሥርዓት የምትተዳደር፣ ብዙ የወርቅ ማዕድናት የሚገኙባት፣ ኃይለኞች ነገሥታት የሚነገሱባት ሀገር እንደኾነች ተጽፏል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ታላቅ እና ኃይሎኞች ናቸው፡፡ ለወዳጆቻቸው ደግነታቸውን፣ ለጠላቶቻቸው ደግሞ ጀግንነታቸውን፣ አይደፈሬነታቸውን የሚያሳዩ ኩሩ፣ ጥንቁቅ እና ረቂቆች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ እውቀት ያላት ስልጡን ሀገር፤ ሕዝቧ ከሌሎች አፍሪካውያን ተለይቶ ሰልጥኖ የተገኘ፣ ዜጎቿ ታማኝ አርበኞች፣ መኳንንቶቿ በውጊያ ጊዜ እጅግ ጀግኖች በድል ጊዜ ደግሞ አዛኝ እና መሐሪ ናቸው ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዶናልድ ሌቪን ፖርቹጋላዊውን ጸሐፊ አልቫሬስን ጠቅሰው ሲጽፉ ኢትዮጵያውያን ፍትሕ የሚታያቸው፣ ቅንነት ያላቸው፣ አዋቂዎች አመለ መልካሞች፣ ገሮች፣ ጨዋዎች እና ቸሮች ስለኾኑና ምሕረትም ለማድረግ ስለሚያዘነብሉ ማንኛውንም በደል ይቅር ለእግዚአብሔር ብለው የሚታረቁ ናቸው ብለዋል፡፡
እኒህ ኩሩና አምላካቸውን የሚፈሩ ደጋጎች በሀገራቸው ላይ ጠላት ሲነሳባቸው ደግሞ አብዝቶ የሚጨክን፣ የማይደነግጥ፣ የማይሸበር፣ የጠላቱን አጥንት የሚሰባብር ደንዳና ልብም አላቸው፡፡ ጀግንነታቸውን ማሳየት በሚገባቸው ጊዜ ጀግንነታቸውን፣ ደግነታቸውን ማሳየት በሚሹ ጊዜ ደግሞ ደግነታቸውን የሚያሳዩ ኩሩና ጀግኖች ናቸው፡፡
በየመዘናቱ ጠላቶች በቅኝ ግዛት ሊይዟት አስበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በተባበረ ክንዳቸው፣ አንድነት ባገነነው ግርማ እና ጀግንነታቸው ቅኝ ግዛት ያሰቡትን ሁሉ እንዳልነበር አድርገዋቸዋል፡፡ ጠላቶቻቸውን ድል መትተው በዓለም ፊት ድንቅ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ ከክብር ላይ ክብር፣ ከዝና ላይ ዝና ደራርበዋል፡፡
ዶናልድ ሌቪን በጻፉትና ሚሊዮን ነቅንቅ በተረጎሙት መጽሐፍ ዲዎደረስ የተባለው የታሪክ ሰው ጠቅሰው ሲጽፉ “ብዙ ኃይለኞች ነገሥታት ቢሞክሯቸውም ሙከራቸው አልተሳካለቸውም፡፡ ካምቢስ ኃይለኛ ጦር ሠራዊት አስከትቶ በእነርሱ ላይ መዝመቱ ለሱም ለራሱም ነፍስ መጥፋት ኾነ፡፡ ለሠራዊቱም መደምሰስ አደገኛ ነበር፡፡ እንዲሁም በድል አድራጊነቷ በጦር ሥልት እውቀቷ ዝነኛ የነበረችው ሰሚራሚስ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ጥቂት ከገባች በኋላ ያን ሀገር ድል አድርጎ መያዝ መቅኖ እንደሌላው ወዲያው ተረዳችው” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባዕድ ንጉሥ ግዛት የማታውቅ ነጻ እና ሉዓላዊት ሀገር ናት፡፡ የአፍሪካ ሀገራት በሙሉ በባዕዳን ኃያላን ቀንበር ሥር እየወደቁ በሚሄዱበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ተከታትሎ የመጣባቸውን ወረራ ሁሉ ድል ይነሱ ነበር፡፡ ነጻነታቸውን ጠብቀው ለመኖር በጀግንነት የሚዋጉ፣ ለነጻነት ሸብረክ የማይሉ ኩሩና ጀግኖች ናቸውና ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የነጻነት ምሽግ ናት ትባላለች፡፡
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በዘመናቸው አያሌ ታሪኮችን የጻፉ፣ ገናና ነን ብለው ለቅኝ ግዛት የመጡትን አውሮፓውያንን ያሳፈሩ የጀግና መለኪያዎች ናቸው፡፡ ዓድዋን የመሠለ የታሪክ ተራራ ያቆሙ፣ የታሪክ ብርሃን ያበሩ፣ ከዓድዋ አስቀድሞም፣ ከዓድዋ በኋላም እጹብ ድንቅ ያስባለ ታሪክ የሠሩ ጀግኖች ናቸው፡፡ የዓድዋን ድልና ሌሎች የኢትዮጵያን አያሌ ድሎች ያመጡት ደግሞ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ጀግኖች፣ ወቶአደሮች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ( ከ1847 እስከ 1983) በተሰኘው መጽሐፋቸው በቅርብ ዘመን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዝናን የሰጠ ድርጊቶች ማሰብ ያዳግታል ይላሉ፡፡ የቅኝ አገዛዝን ማዕከል የገታ አንድ ትልቅ ድርጊት እንደመኾኑ ሁሉ የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረውን ያህል የተገዦቹን አንገት ደግሞ ከተደፋበት ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል የነጻነትና የክብር ፈና ኾነች፡፡ ቀድሞውንም ቢኾን በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የምትወሳው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያኒዝም እየተበላ ለሚጠራ ከነጮች ተጽዕኖ ነጻ የኾነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንስኤ ኾና ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዓድዋ ድል አማካኝነት ቀድሞ በረቂቁ ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ስጋና ደም ተላብሳ ታየች ብለው ጽፈዋል ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፡፡
ኢትዮጵያን በየዘመናቱ የጠበቋትና የሚጠቋት ነበሩ፡፡ አሉ፡፡ ይኖራሉ፡፡ ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በመንግሥትነት ታሪክ ዘመን ሁሉ እንደኖረች አያከራክርም፡፡ ወገንም ጠላትም የተቀበለው ሐቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነቷ ኖራለች፡፡ ወደፊትም ትኖራለች ብለው ጽፈዋል፡፡ የውጭ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለማጥቃት ቢቻልም ለመያዝ ሞክረዋል፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያውያን ድል እየተመቱ ወደየመጡበት ተመልሰዋል ነው የሚሉት የታሪክ ጸሐፊው፡፡
ተድላ ዘዮሐንስ ኢትዮጵያን በነጻነት ጠብቀው ያቆዩዋትን ነገሮች ሲጽፉ “ ኢትዮጵያን በነጻነት ጠብቆ ያቆያት እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራ የኖረችው በልጆቿ ደም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ታላቁ ችግራቸው እርስ በእርሳቸው አለመስማማትና አለመተባበር ነው፡፡ ኾኖም የሚለያዩትና እርስ በእርሳቸው የሚጋጩት በሰላም ጊዜ ነው፡፡ የውጭ ወራሪ በመጣ ጊዜ የእርስ በእርስ ጠባቸውን ወደ ጎን በመተው የመጣባቸውን ጠላት ተባብረው ይመልሳሉ፡፡ ኢትዮጵያን በነጻነት ለማኖር ከረዱት ነገሮች አንዱ ዘውድ ነው፡፡ በሰላም ጊዜ የዘውድ አገዛዝ ተጽዕኖው ከባድ ነው፡፡ የውጭ ወረሪ በመጣ ጊዜ ግን ሕዝቡን አንድ በማድረግ ረገድ ያለው ችሎታ ጽኑዕ ነው፡፡ ነገሥታቱም ብዙ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ነጻነት በመጠበቅ በኩል ዘውድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ለኢትዮጵያ ነጻነት ደጀን ኾኖ ያገለገለው የመሬት አቀማመጥ ነው፡፡ ለምነቷ ብዙ ጠላት አፍርቶባታል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አቀማመጧ ለነጻነት በተደረገው ተጋድሎ በጎ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡” ብለዋል፡፡
ቅኝ ግዛትን ተናንቃ በነጻነት ኖራለች፡፡ ይሄም ጥሩ ታሪክ የሌላቸውን ሀገራትን ያስቀናቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለጥቁሩ ሕዝብ መልካም አርዓያ ናት ብለዋል ተድላ ዘዮሐንስ፡፡ ይህ የጀግንነት፣ የአይደፈሬነት፣ የሉዓላዉነትና የነጻነት ውርስ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ አበው ለልጅ እያወረሱ፣ ልጆችም የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን እያነሱ በየመዘናቱ ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለሠንደቋ ፍቅር ሲዋደቁ ኖረዋል፡፡ ዛሬም እየተዋደቁ ነው፡፡ መነሻቸው እና መድረሻቸው የሀገር ክብርን ማስጠበቅ የኾኑ የቁርጥ ቀን ልጆች ዛሬም በየዱሩ፣ በየሸንተረሩ፣ በየጠረፍ ሀገሩ ሁሉ ስለ እርሷ ክብር ይቆማሉ፤ ስለ እርሷ ክብር ደም ያፈስሳሉ፣ አጥንት ይከሰክሳሉ፤ ያለ ስስት ትክ የለሽ ሕይወታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች ወታደሮች የኢትዮጵያ መከታዎች፣ አለኝታዎች፣ ታሪክና ነጻነት ጠባቂዎች፣ ሉዓላዊነትን አስከባሪዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ልጆች፣ ስለ ኢትዮጵያ ብለው ምሽግ ውለው ምሽግ የሙያድሩ ወቶአደሮች የታላቅ ሀገር መከታ፣ የታላቅ ሕዝብ አለኝታዎች ናቸው፡፡ ቃላቸውን ጠብቀው፣ ሠንደቅ ዓላማዋን አስቀድመው ለክብሯ ይገሰግሳሉ፤ በጀግንነትም ይጠብቃሉ፡፡
የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ ያስቀድሙ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ የኢትዮጵያ ጠባቂዎችና የማስበሩ አጥሮች ክብር ቢሰጣቸው፣ እጅ ቢነሳላቸው፣ በየቀኑ ስለ ጀግንነታቸው ቢነገርላቸው የሚያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደሉም፡፡ ስለ ምን ቢሉ እነርሱ ሀገርን ከሕወታቸው አስበልጠው ይወዳሉ፣ ስለ ሀገር ክብር በጽናት ይኖራሉ፤ ሕይወት ሰጥተው ያኖራሉና፡፡
ወገኔ ብትችል ሀገርህን ኢትዮጵያን ጠብቃት፣ ባትችል ግን ጠባቂዎቿን አትንካባት፣ ሠንደቋን አስቀድመው የወጡት ክብሯን ለመጠበቅ፣ ድንበሯን ለማጥበቅ፣ ታሪኳን ለማድመቅ ነውና፡፡ ከራስ በፊት ለሀገርና ለሕዝብ መሰጠት ጌጣቸውና ክብራቸው የኾኑ ጀግኖች ናቸውና፡፡ እነርሱን አክብራቸው፤ አብዝተህም ውደዳቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!