
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ ወንዙን በፍትሃዊ ለመጠቀም የተደረገው የረጅም ጊዜ ትግል ለፍሬ የበቃበት መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባት “የዓባይን ውኃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም የተደረገው ረጅም ጉዞ ፍጻሜ ነው” ብለዋል፡፡ ስምምነቱ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ በጋራ የውኃ ሃብቶች አስተዳደር እና አጠቃቀም ላይ ፍትሃዊነትን እንደሚያረጋግጥም አጽዕኖት ሰጥተዋል፡፡
“ዕለቱ በዓባይ ተፋሰስ ላይ እውነተኛ ትብብር ለመፍጠር ያደረግነው የጋራ ጥረት ታሪካዊ ምዕራፍ ኾኖ ይታወሳልም” ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ለሰሩ የስምምነቱ አባል ሀገራት “እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል፡፡
ስምምነቱን ያልፈረሙ ሀገራትም ለፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም በመገዛት “የናይል ቤተሰብን“ እንዲቀለቀሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!