
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ዛሬ ዛሬ እየጠፉብን ካሉ እሴቶቻችን መካከል አንዱ ችግር ሲደርስበት ሌላው ነገም በኔ ሊደርስ ይችላል ብለን ማሰብ ነው፡፡ ለችግሩም መፍትሄ፤ ለችግረኛውም እገዛ የማድረግ ባሕላችን እየተዳከመ ነው፡፡ ከመተዛዘን እና ከመረዳዳት ይልቅ በችግረኛው መሳለቅ እና መፍረድ ሲቀናን ይስተዋላል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭትም የሚታየው ይሄው ነው፡፡ ችግሩ በውይይት ተፈትቶ ሰላም እንዲወርድ ከመመኘት ይልቅ በለው እና ግፋ የሚለው ድምጽ አሁንም ጎላ ብሎ ይሰማል፡፡
በዚህ አሰቃቂ ሂደት በርካቶች ለአካላዊ ስቃይ እና ሞት ብሎም በርካቶች ለሃዘን እና ሰቆቃ እንደሚዳረጉም አናስተውልም፡፡
“በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት” እንዲሉ ለራሳችን ያልተገባ ፍላጎት መሳካት የሌሎች ስቃይ እና ሞት እንዲቀጥል የመገፋፋታችን ጉዳይ ነግ በኔን አስዘንግቶናል።
በመጀመሪያ የምንደግፈውም ኾነ የምንነቅፈው ሃሳብ በሰላም እና በውይይት ማሸነፍ እንደሚችል ረስተናል፡፡ ሲቀጥል በጦር መሳሪያ ብቻ ማሸነፍን ማሰባችን የአስተሳሰባችን ጉድለት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እኛ በማናደርገው እና በማንደፍረው ችግር ውስጥ ሌሎች ገብተው እየተሰቃዩ ፍላጎታችን እንዲያሳኩልን መፈለጋችን ሰክነን ያለማየታችን ጥግ ያሳያል፡፡
የሚፈጠር የኑሮ ውድነት እና የማኅበራዊ ግንኙነት መስተጓጎልን እያማረርን፣ መንገድ መከፈትን እና የኑሮ መርከስን እየናፈቅን በሌሎች አካባቢዎች ግን ግጭቱ እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡
በግጭቱ የሚሞቱት፣ ሠርቶ ለመኖር የሚቸገሩ እና የሚሰደዱትን ወገኖቻችን ችግር ልንረዳላቸው አልቻልንም። የምናስበው ግጭቱ በሩቁ እንዲቀጥል እንጅ የንጹሐን ስቃይ አልታወሰንም ወይም ግድ አልሰጠንም።
በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው በየአካባቢያችን የሚመጡ ወገኖቻችን ወደው እና ፈቅደው የተሰደዱ፣ ደልቷቸው የመጡ ይመስል ቤት ኪራይ እና የሸቀጥ ዋጋ በማስወደድ በችግራቸው ላይ ሌላ ችግር እንጨምራለን። ግጭቱ በሰላም ካልተፈታ እየሰፋ ሰላማዊ ነው ባልነው አካባቢያችን ይደርሳል፡፡ ተሸናፊም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል እልህ ይዞ ይጠፋል፡፡ ግጭቱ በአሸናፊ ተሸናፊነት ቢቋጭ እንኳ ሕዝብ እና ሀገርን ጎድቶ ያልፋል፡፡ ሌሎችን ያደፋፈርንበት ጦርነት በአካባቢያችን ሌሎችን ያበረታታንበት ግጭት ለራሳችን መትረፉ አይቀርም፡፡
ዛሬ ሰላም እንዲፈጥሩ ከልባችን ባልጠየቅናቸው ተፋላሚ ወገኖች ምክንያት ሰላማቸውን ሲያጡ ባላዘንላቸው፣ ሲጎዱ ባላገዝናቸው፣ ሲሰደዱ ባላስተናገድናቸው፤ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው መከራ “ነግ በኔ” በማለት ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ግፋ በለው በማለት የሰዎችን ስቃይ ከማራዘም ብሎም ሞትን ከመጥራት ይልቅ ለሰላም መሥራት እና ተፋላሚ ወገኖች ሰላም እንዲፈጥሩ ማሳመን፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ሰላማዊ ወገኖች ከቻልን ማገዝ ይገባል፡፡
አበው “ብልህ በሌሎች ይማራል” እንዲሉ በውስጥ ግጭት ምክንያት ሀገራት ሲፈርሱ ዜጎቻቸው በስደት ሲንገላቱ ከምናየው እና ከምንሰማው መማር ይኖርብናል፡፡ ከኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ሶማሊያ እና ሱዳን ትምህርት ወስዶ ልዩነትን ማጥበብ እና በሰላማዊ መንገድ በውይይት ብሎም በድርድር በመፍታት ሰላምን ማጽናት ይገባል፡፡
ግጭቱን ባለመደገፍ ገለልተኛ መኾን ብቻም ሳይኾን የሰላም እጦቱ ይመለከተኛል በሚል ኀላፊነት ለሰላም ሳይሰለቹ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ሰላም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!