
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕልም ጉልበት፣ ለእምርታዊ እድገት ” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳር ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም፣ ታላቁ የዓባይ ድልድይና በጣና ዳርቻ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች ደግሞ የሚጎበኙ የልማት ሥራዎች ናቸው።
በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሕዝብን የዓመታት ጥያቄዎች የመለሱ ናቸው ተብሏል። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬምን ለሠልጣኞች እያስጎበኙ የሚገኙት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ እርዚቅ ኢሳ የካፍና የፊፋን የጥራት ደረጃ በሟሟላት በተለያዩ ሀገራት የሚንገላታውን ብሔራዊ ቡድን ለመመለስ አልሞ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ስታዲዬሙ ተጨማሪ ገቢ እንዲኾን ታሳቢ ተደርጎ አየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል። የስፖርት ቱሪዝም እንዲያድግ፣ የስፖርት ቤተሰቦች ወደ ከተማ እንዲመጡ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
የመልበሻ ክፍሉን፣ የመጫወቻ ሜዳውን፣ የደጋፊ መቀመጫ ወንበር እና ሌሎች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ለክልሉ ትልቅ ሃብት መኾኑንም ገልፀዋል።
የተመልካች ወንበሮች እየተመረቱ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ስታዲዬሙ ለተመልካች ምቹ እና ማራኪ ኾኖ እየተገነባ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም ትልቅ አሻራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!