የባቡር ሀዲድ ብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ ።

33

ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ 020 ቀበሌ የሚያቋርጠውን የኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ሀዲድ ዋና መስመር መገጣጠሚያ ብረቶች ተደራጅተው በመዝረፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የወረዳው ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የጸጥታ ስምሪት ቡድን መሪ ሽመልስ አወል እንደገለጹት ከኅብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ መሠረት የጸጥታ ኃይሎች ባደረጉት ክትትል ግለሰቦቹ ተይዘዋል።

ድርጊቱን በማስተባበር እና በመምራት የተጠረጠረው የቡድኑ መሪ አምስት የቀን ሠራተኞችን በመቅጠር፣ ጫካ ውስጥ መጠለያ በማዘጋጀት እና ውሎ አዳራቸውን እዚያው በማድረግ በባቡር መሠረተ ልማቱ ላይ ውድመት እና ዘረፋ ፈጽሟል ተብሏል።

የጸጥታ ኃይሉ ከቀበሌ አመራሩ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

በወቅቱም ከ1 ሺህ 240 በላይ የሚኾኑ የምድር ባቡር መገጣጠሚያ ብረቶች ከሰባት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀብሩ ወረዳ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እየተሠራ እንደኾነም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአማራ ክልል የሩዝ ምርታማነት ትልቅ ተስፋ ያለው መኾኑን ገለጹ።