
ሰቆጣ: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አፈጻጸም እና የ2017 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ እቅድ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ “ብዝጎነት እና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት የተካሄደ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶችም በክረምቱ መርሐ ግብር የከወኑትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። ለዚኽም መንግሥት እና ባለሃብቱ የግብአት እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ቢኒያም ዋለልኝ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማራ ወጣት ነው። ደም በመለገስ፣ የተቸገሩ ኅጻናትን በመደገፍ እና አረጋዊያንን በማገዝ “ተስፈኞቹ” ከተባሉ ወጣቶች ጋር እንደሚሰራ ገልጿል። በቀጣይም “ሰው ለሰው” ነውና የተለመደውን የበጎ አገልግሎት ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁሟል።
መንግሥት ለወጣቱ እውቅና መስጠቱ በቀጣይ ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያበረታታ እንደኾነ የገለጸችው ደግሞ ወጣት ዘውድ አወጣ ስትኾን በበጋውም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ እና ደም በመለገስ ሥራ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ መዘጋጀቷን ተናግራለች።
በክረምቱ ወቅት የተበላሹ መንገዶችን በመጠገን፣ የአቅመ ደካማዎችን ቤት በመሥራት፣ በሰላም እና ጸጥታው ዘርፍ ሲሠሩ እንደነበር የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ ወጣት አክሊሉ ወልዴ ገልጿል።
ወጣቱ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠቱ የዋግ ኽምራን ሰላም በአንጻራዊነት ከማስቀጠሉም ባሻገር ባሕላዊ ጨዋታዎች እና መንፈሳዊ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከጸጥታው ዘርፍ ጋር በመኾን የተሠራው ሥራ የሚበረታታ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ሦስት የወጣቶች አደረጃጀቶች ያሉ ሲኾን ወጣቶች ፌዴሬሽን፣ ወጣቶች ማኅበር እና የሴቶች ሊግ በሚል ተደራጅተው ባለፉት ሦስት ዓመታት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ጽኅፈት ቤት ኀላፊ ሚካኤል ሲሳይ ገልጸዋል።
ከ500 በላይ ወጣቶችን በማደራጀት በክረምቱ በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሠሩ የመንገድ ጠረጋ፣ የችግኝ ተከላ እና በሰላሙ ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች የሚያበረታቱ እንደነበሩ አቶ ሚካኤል ሲሳይ ተናግረዋል።
ሰላም ከሌለ ወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ አይሠሩም ነበር ያሉት ኀላፊው ከአልባሌ ቦታ በመውጣት በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
የሰቆጣ አስተዳደር አመራርም ከወጣቱ ጎን በመኾን እንደሚሠራ የገለጹት ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ክልላችን ላይ የሚስተዋለውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ወጣቱ ለሰላም ቁርጠኛ ሊኾን ይገባል ብለዋል።
በቀጣይም በ13 ዘርፎች ማለትም በአረንጓዴ አሻራ፣ በሰላም፣ በመንገድ፣ በደም ልገሳ እና በሌሎችም በመሳተፍ በበጋውም የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል አቶ ጌትነት።
በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም በዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወጣቶች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች እና ተቋማት የእውቅና ሽልማት ከከንቲባው ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!