የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አሳሰቡ።

33

ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያካበተውን ልምድ በሚመጥን መልኩ በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ምሩቃን ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ ሚኒስትሮች በርካታ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ታሪክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ አበርክቶ፣ ስምና ዝናም እንዳለው አንስተዋል።

በረጅም ዓመታት ልምዱ በርካታ የምርምር ስራዎችን በማበርከትና ምሁራንን በማፍራት የሀገር ባለውለታ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ያካበተውን ልምድ በሚመጥን መልኩ በትምህርት፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ከ49 አመታት በፊት የዚሁ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበርኩ ያሉት ፕሬዝዳንቱ የቆይታቸውን ትውስታ በመድረኩ ለታደሙ የቀድሞ ምሩቃን አካፍለዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ለዩኒቨርሲቲያቸው የላቀ እድገት አሁንም አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው አንስተው በመንግስትም በኩል አስፈላጊው ድጋፍና እገዛ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግብርና መስኩን ለማዘመን የምርምር ተቋማትን መደገፍና ማዘመን ይገባል” አቶ አሸተ ደምለው
Next articleየበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አጠናክረው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።