
ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና ምርምር ማዕከል በዘንድሮው ዓመት ከአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር የለማ የማሽላ እና የሰሊጥ የዘር ብዜቶችን የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
በጉብኝቱም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው እና የዞኑ ግብርና መምሪያ እንዲሁም የሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል የሥራ ኀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
“ያለውን ችግር ተቋቁመን የዘር አጠቃቀም ችግሮችን ለመፍታት የዘር ምርምር በማድረግና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራን ነው” ያሉት የዞኑ ግብርና ምርምር አስተባባሪ አቶ ሚኒስትር ብርሃኔ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚሆን 140 ሄክታር መሬት ማሽላና 45 ሄክታር መሬት ሰሊጥ ሰብል በምርምሩ ማዕከል መልማቱን አብራርተዋል።
የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር እያለሙ መሆናቸውን ያነሱት አሰተባባሪው ይህም በዞኑ ያለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት የተባዛው የምርጥ ዘርም ጥናት ተካሂዶበት የምርጥ ዘር ሰርትፍኬትን ካገኘ በኋላ ለገበሬው ተደራሽ እንደሚሆን ገልፀዋል።
በግብርና ምርምሩ የሚደረገው የዘር ብዜት ምርጥ ዘርን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም አለው ያሉት የዞኑ ግብርና መምሪያ ተወካይ ኃላፊ በሪሁን ፀጋዬ ለኅብረተሰቡም እንደተሞክሮ በመሆን የሚያገለግል መሆኑን አንስተዋል።
የምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥና ለውጭ ሀገር ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረትም የግብርና ምርምሩ የሚሰጠው ፋይዳ የላቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ሁሉም አካል ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል። የግብርና መስኩን ለማዘመን የግብርና ምርምር ማዕከል ተቋማትን መደገፍ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።
የሁመራ ግብርና ምርምር ማዕከል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሁኖም እያደረገ ያለው የምርጥ ዘር ብዜት የሚደነቅ ነው ሲሉም አመሥግነዋል።
ግብርና የኅልውናችንና የእድገታችን ማስቀጠያ መንገድ ነው ያሉት አቶ አሸተ ይንን ዘርፍም ወደተሻለ ከፍታ ለመውሰድ ከምን ጊዜውም በላይ እንደሚሠሩ አስገንዝበዋል።
የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመለክተው የምርምር ማዕከሉ እየሠራው ያለውን ሥራ እንዲያስቀጥል አስገንዝበዋል። ለዚህ መሳካትም አስተዋፅኦ ላደረጉት አካላት ምሥጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም ለምርምር ማዕከሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!