የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የሸቤልለይ ሪዞርት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

38

ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተገነቡ የሚገኙ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የኾነው የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ ያለበትን ደረጃ ዛሬው እለት መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

ከጅግጅጋ 25 ኪሜ ርቀት ላይ በፋፈን ዞን ሸቤልለይ ወረዳ የተጀመረው የሸቤልለይ ሪዞርት ግንባታ 10 ወራት ያስቆጠረ ሲሆን በውስጡ ለቱሪስት መስህብ የሚያገለግሉ 8 ዘመናዊ መንደሮች፣ 3 ሰው ሠራሽ ግድቦች፣ ለመንደሩ የሚያገለግል 13 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፋልት ግንባታና የውኃ፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም ሙሉ መሰረተ ልማት ተሟልቶለታል ብለዋል።

አቶ አደም በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ እድልን እንዲሁም ለከተማው መነቃቃት ከመፍጠሩም በላይ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር ታስቦ በመገንባቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ለጎረቤት ሀገራት ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ እንደሚሆንና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አምናለሁ።

በተለይም ከበርበራ እስከ ውጫሌ፣ ከጅግጅጋ እስከ ጅቡቲ በመሠራት ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከሸቤልለይ ሪዞርት ጋር ተጣምረው ጅግጅጋ ከተማን ከፍተኛ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጓት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን እየሠሩ ያሉ የፌደራል እና የክልሉን አመራሮች እንዲሁም ተቋራጭ ድርጅቶችን አመሥግነዋል።

ፕሮጀክቱ ከፍፃሜ እንዲደርስ ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዋልያዎቹ ዛሬ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን በሊሴ ሞደርን ዲ’ኮኮዲ ሜዳ አከናውነዋል” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
Next article“የግብርና መስኩን ለማዘመን የምርምር ተቋማትን መደገፍና ማዘመን ይገባል” አቶ አሸተ ደምለው