“ዋልያዎቹ ዛሬ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዳቸውን በሊሴ ሞደርን ዲ’ኮኮዲ ሜዳ አከናውነዋል” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

56

ባሕር ዳር: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 8 ሶስተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከጊኒ ጋር ታከናውናለች።

የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ኮትዲቭዋር በሚገኘው ኢቢምፔ ኦሊምፒክ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 8 እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ሲሸነፍ፣ ከታንዛንያ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።
ውጤቶቹንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በ49 ዓመቱ የጊኒ እና ፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ባለው ጊዜያዊ አሠልጣኝ ቻርልስ ፓኩዌሌ የሚመራው የጊኒ ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በታንዛንያ 2 1 ለ እንዲሁም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 1 ለ 0 ተሸንፏል።

ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ አራተኛ ደረጃ ይዛለች።

ዋልያዎቹ ዛሬ ከጊኒ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ አስቀድሞ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ትናንት በሊሴ ሞደርን ዲ’ኮኮዲ ሜዳ ማከናወናቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

22 ተጫዋቾች ልምምድ ያከናወኑ ሲሆን አጥቂው ቢንያም በላይ ከጉዳት ባለማገገሙ በልምምዱ ላይ አለመሳተፉ ታውቋል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በማጣሪያው የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

የ36 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ ክሌመንት ፍራንክሊን ፓን የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ኢትዮጵያ እና ጊኒ የምድብ አራተኛ ጨዋታቸውን ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በኢቢምፔ ኦሊምፒክ ስታዲየም ያደርጋሉ።

ዋልያዎቹ ከኦዞዎቹ ጋር የሚያደርጓቸው የማጣሪያ ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፋቸውን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም አላቸው።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ 8 ከትናንት በስቲያ በተደረገ ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታንዛንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ኢዜአ እንደዘገበው ውጤቱን ተከትሎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነጥቧን ወደ ዘጠኝ ከፍ በማድረግ የምድብ መሪነቷን አጠናክራለች።ታንዛንያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት ከጊኒ አቻው ጋር ይጫወታል።
Next articleየገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አካል የሆነው የሸቤልለይ ሪዞርት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።