በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ ምርምሮች ለፈጠራ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ዩኒቨርሲቲው ገለጸ።

52

ደሴ: ጥቅምት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራዎች ወርክሾፕ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ውጤማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ነው በወርክሾፕ የተገለጸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የዓባይ አዋሽ ተፋሰስ የጥናት እና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ወንድዬ ያረጋል (ዶ.ር) ተቋሙ የተለያዩ የምርምር ጹሑፎችን በማቅረብ በጀት በማፈላለግ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ውኃን በተመለከተ ችግር ፈች የኾ ሥራ እየተካሄደ መኾኑን በማንሳት ሥራው ሲጠናቀቅም ለፖሊሲ አውጭዎች እና ለመንግሥት አሥፈጻሚ አካላት በግብዓትነት ያገለግላል ነው ያሉት፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ሰለሞን ጎራው ለዜጎች ነጻ የሕግ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ከዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተለይም ከተፈናቃዮች ጋር የተያያዙ የሕግ አገልግሎት ሥራዎች መከናወናቸውን በተሞክሮነት አንስተዋል፡፡

ከሚዲያ አካላት ጋር በመተባበርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት አቶ ሰለሞን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የምርምር እና የቴክኖሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰይድ ሁሴን (ዶ.ር) ለተመራማሪዎች የሥራ ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ለማኅበረሰቡ ችግር ፈች የኾኑ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ ምርምሮች ከውጭ ገንዘብ ከማስገኘት ባለፈ ለፈጠራ እና ቴክኖሎጅ ወሳኝነት እንዳላቸው የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡

የተካሄደው ወርክሾፕ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የፕሮጀክት ጹሑፎችን በማቅረብ ያሉ ልምዶችን በማጠናከር እርስ በእርስ ልምድ የሚወሰድበት መድረክ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች መማር ማስተማሩን ማገዝ፣ ሃብት ማፈላለግ፣ ፈጠራን ማስፋፋት በትኩረት የሚሠራባቸው ዘርፎች በመኾናቸው ተጠናረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የተግባር ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመኾኑ ከኢንዱስትሪዎች እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ማኅበረሰቡ ላይ ችግር የሚፈቱ ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ተወያዩ።
Next articleበባሕር ዳር የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለቱሪስቶች ምቹ ከተሞች ግንባታ ማረጋገጫ መኾናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገለጹ።