ኢትዮጵያ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ እንድትኾን እንደሚሠራ የኮሙዩኒኬሽን ሚንስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሣ ገለጹ።

68

ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሣ በሰጡት መግለጫ በመስከረም እና ጥቅምት ወራት በርካታ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት በአደባባይ እንደሚከበሩ ገልጸዋል። እነዚህን በዓላት ለቱሪዝም ዘርፉ መጠቀም እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

በጥቅምት ወርም አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃሉ ብለዋል። በወሩ ከሚጠበቁት መካከልም ዓለም አቀፍ እና አሕጉራዊ ኮንፈረንስ ውስጥ ”ከረሃብ ነጻ ዓለም” በሚል በአዲስ አበባ ከጥቅምት 26 እስከ 28 በሚደረግ ኮንፈረንስ በርካታ ዓለም አቀፍ እንግዶች እንደሚሳተፉ ጠቅሰዋል።

በዚህ አጋጣሚም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት እና በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ልምድ ታካፍላለች ብለዋል። ከጥቅምት 9 እስከ 12 ድረስ የሚካሄደው የአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሥብሠባ ሌላኛው ኹነት ነው ያሉት ሚንስትር ድኤታዋ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀች ያላትን ፍላጎት በማጠናከር ዕቅዱን ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

ሦስተኛው የአፍሪካ የመከላከያ ሚንስትሮች ጉባኤም ከጥቅምት 5 እስከ 7/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ለሰላም እና መረጋጋት ያላትን ሚና የምታሳይበት ይኾናልም ብለዋል። ሁሉም የሥብሠባ ታዳሚዎች በሀገር ደረጃ የተሠሩ ሥራዎችን ስለሚጎበኙ ለቱሪዝም ኮንፈረንስ ከፍተኛ አበርክቶ አለው ነው ያሉት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮንፈረንስ ቱሪዝም በቢሊዮን ዶላር የሚለካ ገንዘብ እንደሚንቀሳቀስ እና ኢትዮጵያም ከዚህ ተጠቃሚ እንድትኾን በጥቅምት ወር በሚኖሩ ኹነቶች ላይ አተኩሮ ይሠራል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአፈ ጉባዔና ቋሚ ኮሚቴዎች የምክር ቤቶችን ተልዕኮዎች በሚገባ ተገንዝበው ጠንካራ ምክር ቤት መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ተወያዩ።