
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት ከተዋረድ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር በኃላፊነታቸው እና ተልዕኮዎቻቸው ላይ ሥልጠና ተሰጥቷል።
አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሥልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለፁት አፈ ጉባዔዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች የምክር ቤቶችን ሚናና ተልዕኮዎች በሚገባ ማወቅና ጠንካራ ምክር ቤት መገንባት እንደሚገባ ገልፀው ሕግ ማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር ተግባር ማከናወን እና የሕዝብ ውክልናን መወጣት የምክር ቤቶች ዋና ዋና ተልዕኮዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተዋረድ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በክትትልና ቁጥጥር ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ተቋማት የተሰጠን ተልዕኮ ማዕከል በማድረግ እና ያዘጋጇቸው እቅዶች ሲፈፀሙ የነበሩ የአፈፃፀም ሂደቶች እና የበጀት አጠቃቀምን እንዲሁም ኅብረተሰቡ እየተሳተፈ እና እየተጠቀመ መሆኑን በአግባቡ ማየት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አኹን ያለንበት ነባራዊ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ችግሩ ሰፊ ነው በሚል የሚነሳ ምክንያት እንደሚኖር አንስተው፤ የሕዝብ ውክልናችንን መሰረት በማድረግ ያለብንን ኃላፊነት መሰረት ያደረገ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለአሚኮ በላከው መረጃ በዚህ ሥልጠና ከሚገኘው ግንዛቤ በመነሳት ጠንካራ ምክር ቤት በገንባት የሕዝቡን አመኔታ ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!