“የአፍሪካ ተወዳዳሪነት እየተፈተነ ያለው በጂኦፖለቲካ እና ጂኦኢኮኖሚ ባለው ዓለም አቀፍ ፍትጊያ ምክንያት ነው” የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት

46

አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ)አፍሪካ ያለባትን የአንድነት ችግሮች ለመቋቋም እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተሻሉ መፍትሔዎች እና ፖሊሲዎችን መጠቀም እንደሚገባት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከአልጀዚራ የጥናት ማዕከል ጋር በመኾን የአፍሪካ የአንድነት ችግሮችን ለመፍታት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ ኮንፈረንስ እየተካሔደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃዕፋር በድሩ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአፍሪካ ተወዳዳሪነት እየተፈተነ ያለው በጂኦፖለቲካ እና ጂኦኢኮኖሚ ባለው ዓለም አቀፍ ፍትጊያ ምክንያት ነው ብለዋል። ይህም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ፖለቲካ ወደ ኋላ የጎተተ እንደኾነ ነው ያብራሩት። በዚህም የአፍሪካን ዕድገት ፍላጎት ለማስከበር መትጋት ይገባል ብለዋል።

በዚህ ኮንፈረንስም አፍሪካ ከቀጣናዊ፣ ከአካባቢያዊ፣ ከዓለማቀፋዊ ግንኙነቶች እና ውድድሮች ጎን የተሻሉ ፖሊሲዎችን እና መፍትሔዎችን ለመቅረጽ የሚረዳ የፖሊሲ አውጭዎች እሳቤ ይቀመራል ብለዋል። ኮንፈረንሱ በአፍሪካ ውስጥ ስላሉ የድንበር ይገባኛል አለመግባባቶች፣ የውጭ ኀይሎች በአፍሪካ የሚያደርጉት የኀይል እሽቅድድም፣ ተጋላጭነት እና የማንነት ትግሎች በሚሉ እና በሌሎች ጉዳዮችም እየመከረ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአረጋውያን ለሀገራቸው የከፈሉትን ውለታ የሚመጥን ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሳሰበ።
Next articleአፈ ጉባዔና ቋሚ ኮሚቴዎች የምክር ቤቶችን ተልዕኮዎች በሚገባ ተገንዝበው ጠንካራ ምክር ቤት መገንባት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።