
እንጂባራ: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን አረጋዊያን ለሀገር እና ሕዝብ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በመዘከር፣ እውቅና በመስጠትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በየዓመቱ ይከበራል። የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀንም ለ34ኛ ጊዜ ”ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን” በሚል መሪ መልእክት በእንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።
በበዓሉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የያኔው ወጣቶች የአሁኑ አረጋውያን ሀገራቸውን በእውቀታቸው ያገለገሉ፣ በደማቸውና በአጥንታቸው ጠብቀው ከእነ ሙሉ ክብሯ ያቆዩ የሀገር ባለውለታ ናቸው ብለዋል። እነዚህ የሀገር ባለውለታዎች ጉልበታቸው በደከመ፣ ወረታቸው ባነሰ ጊዜ ከጎናቸው መቆም ደግሞ አሁን ካለው ትውልድ የሚጠበቅ ነው ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አምባነሽ ስሜነህ በበኩላቸው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አረጋውያን የመሥራት አቅማቸውን በሚመጥኑ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ ቀሪ ዘመናቸውን በሰላም፣ በጤናና በፍቅር እንዲኖሩ የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የከተማ ግብርናና የእህል ወፍጮ ዘርፎች፣ አረጋውያን ከተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል እንደሆኑ ያነሱት መምሪያ ኀላፊዋ አረጋውያን በዘላቂነት የሚጦሩበትን የገቢ ማስገኛ ሕንፃ በእንጅባራ ከተማ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል። አረጋውያን ለሀገራቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በሚመጥን መልኩ በዓሉ መከበሩ እንዳስደሰታቸው የገለፁት ደግሞ የበዓሉ ታዳሚ አረጋውያን ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በርካታ አረጋውያን ድጋፍ እንደሚሹና ትውልዱ የአባቶቹን ውለታ መዘንጋት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል። በበዓሉ ማጠቃለያም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር ለተጋለጡ አረጋውያን የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!