“የከንቲባ ችሎት እና አሚኮ አደባባይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የሕዝብን ጥያቄ እያመላከቱ ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

42

ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡ የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በርካታ ሥራዎችን መሥራቱ ተመላክቷል፡፡ ቢሮው ከተሞችን ለነዋሪዎቹ የተመቹ ማድረግ በትኩረት የሚሠራበት ነው ተብሏል፡፡

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በ2016 ዓ.ም የነበረውን ችግር ታሳቢ በማድረግ የ2017 ዓ.ም ዕቅድ መታቀዱን ነው የተናገሩት፡፡ ዕቅዶችን ከፌዴራል ጋር የማናበብ እና ወደ ዞኖች እንዲሁም ወደ ከተሞች የማውረድ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሠራው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የከተማ ፕላን የቀጣይ የከተማን ዘመናዊነት ታሳቢ ያደረገ መኾን እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ ከተሞች የሥራ ዕድል እና የሃብት መፍጠሪያ እንዲሁም የምርታማነት ማዕከላት መኾናቸውን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ነው ያስታወቁት፡፡ ከተሞች የቀጣይ የዓለም ዕድገት ማዕከሎች ናቸውም ብለዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በሰፊው እየተስተዋለ እንደሚገኝ የተናገሩት ኀላፊው የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በጥናት፣ በቀጥታ ከተገልጋዩ በሚገኝ መረጃ እና በምስጢራዊ ምልከታ ችግሮች መገኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሩን ለመቅረፍ የአሠራር ሥርዓትን ማስተካከል እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት፡፡

በተቋሙ 16 የሚኾኑ የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል እና በአዲስ መልኩ ሕግ ማሻሻያዎችን እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአሠራር ሥርዓትን የማዘመን፣ ዲጂታላይዝድ የማድረግ ሥራ መሥራት ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል ነው ያሉት፡፡ የከንቲባ ችሎት እና የአሚኮ አደባባይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ኅብረተሰቡ በከተሞች የሚያነሳቸውን ችግሮች ለማየት ማስቻላቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች በአሚኮ አደባባይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እያዩ መኾናቸው ችግሮችን ለመፍታት የዕቅዳቸው አካል አድርገው እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው ነው ያስታወቁት፡፡ የከንቲባ ችሎት እና የአሚኮ አደባባይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እያጠናከሩ በመሄድ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚጠቀሙባቸውም ተናግረዋል፡፡

የከተማ መሠረተ ልማት በትኩረት እንደሚሠራበት ያመላከቱት ኀላፊው መሠረተ ልማት የሕዝብን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በከተሞች 380 ኪሎ ሜትር መንገዶች መሠራታቸውን ያነሱት ኀላፊው መንገዶችን እንደ አዲስ የመሥራት እና የማደስ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡

ከተሞች የተቀመጠውን የገቢ አሠባሠብ ሂደት በመጠቀም ገቢያቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የኅብረተሰብ ተሳትፎን ማሳደግ በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ የኮሪደር የወንዝ ዳርቻዎችን የማልማት ሥራ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

በከተሞች 3 ቢሊዮን በሚደርስ በጀት 47 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችም እንደሚጠበቁ ነው ያመላከቱት፡፡ ከተሞች ወደ ኮሪደር ልማት ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ እና ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲፈቱ እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡ ተቋማትን በማቀራረብ ችግር እየፈቱ እንዲሄዱ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ወጣቶችን በሰፊው ሊቀጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ከማስፋፋት አኳያ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ ከተሞች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላት መኾን አለባቸው ሲባል ከተሞችን መርታማ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ከተሞች መርታማ ሲኾኑ የወጣት ኀይል ይፈለጋል፤ ሃብት የኾነ እና የሥራ ዕድል ፈጣሪ የኾነን ወጣት በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ እና ሕዝብ የሚያነሳቸው ችግሮችን ለመፍታት ያደሩ እና የቆዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ማስተካከል ይገባል ነው ያሉት፡፡ የአሠራር ሥርዓትን ማዘመን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡ በሩብ ዓመቱ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ጥያቄዎች ስለመፈታታቸውም ነው የተናገሩት፡፡ ችግሮችን የመፍታት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ400 ሺህ በላይ ቡክሌቶችን በማሳተም ለዜጎች ተደራሽ ተደርጓል” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት
Next article“ከ242 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ሥልጠና እየወሰዱ ነው” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት