
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር “የቁልፍ መሠረተ ልማት ደኅንነት ለዲጅታል ሉዓላዊነት!” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ተከብሯል። በክብረ በዓሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሐሚድ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር የተቋማትን እና የኅብረተሰቡን የሳይበር ደኅንነት ንቃተህሊና ለማጎልበት እና የሚቃጣውን ጥቃት ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ውይይት ተካሂዷል። በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሐሚድ አንስተዋል።
የሳይበር ደኅንነት ለአንዲት ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት ፋይዳው የጎላ ይሁን እንጅ የጎንዮሽ ጉዳቱ ዓለምን እየፈተነ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ብቻ በ2015 ዓ.ም 6ሺህ 959 እንዲሁም በ2016 ዓ.ም ደግሞ 8 ሺህ 854 የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን ተናግረዋል። ይሁን እንጅ በተደረገው ቅንጅታዊ አሠራር ጥቃቱን ማክሸፍ መቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።
ይህ አሀዝ የሳይበር ጥቃቱ እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። በመኾኑም ለሀገራዊ ሉዓላዊነት መረጋገጥ አይበገሬ ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት አቅምን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ አሁን ያለው የሳይበር ደኅንነት ለዓለም አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን አንስተዋል።
የሀገራት ሉዓላዊነት በሳይበር ጥቃት እየተፈተነ ነው ብለዋል። ማንኛውም ግለሰብ በቂ ዕውቀት እና ክህሎት ሳይኖረው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅን በመጠቀም በዜጎች እና በቁልፍ መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው ብለዋል። የሀገሪቱን ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ደኅንነት እና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የዜግነት ግዴታ በመኾኑ በማኅበረሰቡ እና በተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይፈጸም በንቃት መከታተል እና መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የጤና፣ የፋይናስ፣ የትራንስፖርት፣ የጸጥታ እና ደኅንነት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ እና ሌሎች ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ከሳይበር ጥቃት መከላከል እንደሚገባ ነው የገለጹት። የሀገሪቱን ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲ እና መመሪያዎችን መቅረጽ፣ የተራቀቁ ተክኖሎጅዎችን መተግበር፣ ቁልፍ መሠረተ ልማት የሚያሥተዳድሩ ተቋማትን ብቁ የሰው ኀይል መገንባት እና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት እንዲሁም የዜጎችን የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
5ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ወር እሰከ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም ይከበራል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!