የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ማዘመን ለሁሉም የተመቸ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አሠራር ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።

31

ባሕር ዳር: መሥከረም 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለ6ኛው የታማኝ የግብር ከፋዮች ሽልማት ተሸላሚዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት “የዜግነት ግዴታችሁን ለመወጣት ያደረጋችሁት ቁርጠኝነት ምስጋና የሚገባው ነው” ብለዋል።

ታማኝነት ከግለሰብ ይጀምራል፤ ግብር መክፈል ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የዚያ እምነት መገለጫም ነው፤ ለበለጠ ጥቅም ሁላችንም የምንካፈለው ግዴታችንም ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ለታማኝነታችሁ መንግሥት የከፈላችሁት ግብር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለጋራ እድገታችን ወሳኝ በኾኑ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባሉ ግዙፍ የሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ አስተዋፅዖችሁን በማዋል ይህንን አደራ ያከብራል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በግብር አሰባሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጦች እየታዩ ቢኾንም፣ ይህን ጥሩ ጅማሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

ሙስናን መቀነስ እና የግብር አሰባሰብ ሥርዓታችንን ማዘመን ለሁሉም የተመቸ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አሠራር ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ለማድረግ እንሠራለን” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው
Next articleሾተላይ ምንድን ነው? እንዴትስ ይከሰታል?