”የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ለማድረግ እንሠራለን” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው

16

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶች የ2017 የሥራ ዘመን በይፋ ተጀምሯል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የ2017 ዓ.ም የሥራ ማስጀመሪያ የንቅናቄ ፕሮግራም አካሂዷል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት ሥርዓቱን ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢ እና ተደራሽ በማድረግ ነጻ የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የፍርድ ቤቶች የሦስት ዓመት የማሻሻያ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቅሰዋል። ግቡም ስድስት ፕሮጀክቶችን መሠረት ባደረገ የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ሥራ ለተገልጋዩ ማኅበረሰብ ተደራሽ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ የዳኝነት ሥርዓት በመገንባት ፍትሕን ማስፈን ነውም ብለዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ በ2017 ዓ.ም ፍትሕን በማስፈን ተዓማኒ ፍርድ ቤት ለመፍጠር ከዳኝነት እና ከፍትሕ አካላት እንዲሁም ከጠበቆች ጋር በለውጥ ፕሮግራሞቹ ላይ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል። በውይይቱም በለውጥ ፕሮግራሞቹ ዙሪያ መግባባት መፈጠሩን እና በቁርጠኝነት ለመተግበር ተነሳሽነት መኖሩን ገልጸዋል።

አቶ ሙሉዓለም በ2017 የሥራ ዘመን ባለድርሻ አካላት የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ለኅብረተሰቡ የተሻለ የዳኝነት አገልግሎት ለመሥጠት የሚሠሩበት እንዲኾንም ተመኝተዋል። በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍርድ ቤቶች የ2017 የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በተደረገ ውይይትም የዳኝነት ሥርዓቱ የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት ስላለባቸው ኀላፊነት፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ስላሉት ዕድሎች እና እየተተገበሩ ስለሚገኙ የማሻሻያ ሥራዎች ተነስቷል።

የባሕር ዳር እና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ኀይለየሱስ አይዞህበል ለ2017 ዓ.ም የፍርድ ቤቶች ሥራ የታዩ ክፍተቶችን አርሞ ለመሥራት አቅጣጫዎች ሲሰጥ የመጀመሪያ መኾኑን ገልጸዋል። ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው ዳኝነት በመስጠት ኅብረተሰቡ የፍትሕ ተጠቃሚ እንዲኾን እንሠራለን ብለዋል። ችግሮችን ለመፍታትም መታቀዱን እና በመፍትሄ አቅጣጫዎችም ላይ ውይይት መደረጉን ነው የተናገሩት። ኅብረተሰቡ የተማረረባቸውን ወንጀሎች ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን። ኅብረተሰቡም ለዳኝነት ነጻነቱ መተባበር አለበት ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ኢትዮጵያ ንጋቱ በመጪው የሥራ ዓመት ራሳችንን አዘጋጅተን ክፍተቶችን አርመን ለመሥራት ተዘጋጅተናል። ኅብረተሰቡን በማገልገልም ኀላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል። በዕለቱ የሰበር ሰሚ ችሎቶች፣ የሰበር አጣሪ፣ የፍትሐ ብሔር ችሎቶች፣ የወንጀል ችሎቶች፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት የዳኞች ምደባም ተደርጓል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምዓንተ አግደው የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ ያሉ የእርቅ እና ሽምግልና አማራጭ የግጭት መፍቻዎችንም በማጠናከር የፍርድ ቤቶችን ጫና ማቃለል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ለዚህም በጥናት የተመሠረተ ሥራ ይሠራል ብለዋል። የፍትሕ ሥርዓቱን በማሻሻልም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት።

ማኅበረሰቡን ስለ ሕግ እና ፍትሕ በማስተማር ትክክለኛ ግንዛቤ ለማስያዝ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እንደሚሠሩም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት። ፍትሕን የሚያሰፍነው የሰው አእምሮ በመኾኑ ለአቅም ግንባታ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለንም ብለዋል። ከዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ጥምረትም ጋር በትብብር በመሥራት ለፍትሕ መስፈን በርብርብ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዲጂታላይዜሽንን በመተግበር በቴክኖሎጂ ተደግፎ በመሥራት ሥራን ማቅለል፣ ፍትሕን ማሳለጥ እና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ፍርድ ቤቶችን ለሥራ ምቹ ማድረግ፣ የሰው ኀይል ማደራጀት እና አቅም የመገንባት ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት ግባችንን መትተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን ማዘመን ለሁሉም የተመቸ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አሠራር ለመፍጠር ወሳኝ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።