“የዛሬውን በውል የምንገነዘብ እና የምንተገብር መሪዎች ነን” ይርጋ ሲሳይ

22

ባሕር ዳር: መስከረም 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕልም ጉልበት፣ ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰጠው የብልጽግና ፓርቲ የስልጠና መርሐ ግብር በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡

በስልጠና በመርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት እና የፓርቲ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ስልጠናው ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ለተመረጡ መሪዎች የሚሰጥ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ዓላማ የአመለካከት እና የተግባር አንድነትን በማጎልበት፣ የመሪዎችን ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ዓላማ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መግንሥት የመገንባት እና ሀገራዊ ሕልምን ለማሳካት እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ትልቅ እና ግልጽ ሃሳብ ያለው ፓርቲ ነው ያሉት ኀላፊው የመሐል ፖለቲካን እንደሚከተልም አመላክተዋል፡፡ መነሻችን መደመር መዳረሻችን ደግሞ ብልጽግና ነው ብለዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም የተሰጠውን ስልጠና በማጠናከር በድጋሜ በዚህ በጀት ዓመት ለመዋቅሩ በተደራጀ እና በተለየ ሁኔታ ስልጠና እየተሠጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት የሚሰጠው የመሪዎች ስልጠና በዓይነቱ የተለየ፣ ብዙ ሃሳቦችን የያዘ፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ትልቅ ተምሳሌት የሚያደርግ፣ ተጽዕኖ የሚፈጥር ሀገር ለመገንባት የሚያስችል፣ ዜጎቿ የሚከበሩባት፣ ሰላም እና መረጋጋት የሚፈጠርባት፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር የገጠመንን ስብራት የምንጠግንበት ትልቅ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡

ፓርቲው ታላቅ ሕልም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ የትናንቱን መልካም እና በጎ ነገር የሚያስቀጥልና አቅም ያለው ፓርቲ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የዛሬውን በውል የምንገነዘብ እና የምንተገብር መሪዎች ነን ብለዋል አቶ ይርጋ በመልእክታቸው፡፡ የነገውን የምንመለከትበት መነጸር እና ረጅም ሕልም ያለን መሪዎችን ነን ነው ያሉት፡፡

ብልጽግና ሪፎርሙ መሬት እንዲነካ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ሪፎርሙ ያጣነውን ዴሞክራሲ ለመትከል፣ የገጠሙንን የፖለቲካ ስብራቶች ለመጠገን፣ የሰው ልጆችን ተደማሪ ፍላጎት ለማሟላት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማረጋገጥ የምንሄድበት ነው ብለዋል፡፡
የውስጣችንን ልዩነት በማጥበብ እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የተጀመረውን የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ተልዕኮ ቅድሚያ ሰጥተን እንሠራለን ብለዋል፡፡ ሁሉም ተግባራት በተቋማት እና በተቀመጠው የሥራ ክፍፍል እንደሚፈጸም ነው የተናገሩት፡፡

ሁሉንም ተግባራት አቀናጅተን ስንመራ ክልሉ የገጠመውን ችግር በአጭር ጊዜ ቀርፈን፣ የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ጥቅም እና የፓርቲውን ተልዕኮ እንፈጽማለን ነው ያሉት፡፡
መሪዎች በሥነ ምግባር እና በሞራል ተምሳሌት ልንኾን ይገባናልም ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንም የሌለው እምቅ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት፣ በአያቶቻችን የተሠሩ ታላላቅ ታሪኮች አሉን ያሉት አቶ ይርጋ እነዚህን እንደመስፈንጠሪያ በመጠቀም ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር አሁናዊ የብልጽግና ጉዞን ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ታላቅ፣ ግዙፍ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ እና የአፍሪካ ተምሳሌት የኾነች ሀገር መፍጠር ግድ ይለናልም ብለዋል፡፡ ስልጣናው የተሳካ እንዲኾን ሰልጣኞች ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

ለሰልጣኞች የገጠምንን የፖለቲካ እና የሰላም ስብራት የሚጠግን እና አቅም በሚፈጥር መልኩ ስልጠናውን እንድትከታተሉም አሳስባለሁ ነው ያሉት። የስልጠናው ግብ ጠንካራ ፓርቲ መፍጠር፣ የተጀመረውን ሪፎርም መሬት ማስነካት፣ የፓርቲውን እሳቤ እና ፍላጎት መረዳት እና መገንዘብ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሕዝብን እርካታ የሚያረጋግጡ ተቋማትን መፍጠር የሁልጊዜ ሥራ እንደሚኾንም ተናግረዋል፡፡ ሰላምን ማረጋገጥ፣ ፍትሕን ማስፈን የሚችሉ ተቋማትን መፍጠር የግድ ይላል ያሉት ኃላፊው ተቋማቱ አቅም ፈጥረው እና ጠንካራ ኾነው ሲቀጥሉ ጠንካራ መንግሥት መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡

አባቶቻችን እና አያቶቻችን ባስረከቡን ሀገር ሃሳብን በመጠቀም በጥንካሬ በመሥራት ለውጭ እና ለውስጥ የማይበገር አቅም መፍጠር ይቻላል ነው ያሉት በመልእክታቸው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሪን ሳንገነባ ሀገር ልንገነባ አንችልም” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት ግባችንን መትተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)