
ባሕር ዳር: መስከረም 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕልም ጉልበት፣ ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰጠው የብልጽግና ፓርቲ የስልጠና መርሐ ግብር በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡
በምርሐ ግብሩ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት እና የፓርቲ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ብልጽግና ፓርቲ የሀገርን የረጅም ጊዜ ሕልም የኾነውን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ትልም ለማሳካት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ራዕይ እና ተልእኮ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካ እና በዓለም ደረጃ ሊኖራት የሚችልበትን ደረጃ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የነበሩ ችግሮችን በመሻገር የሚኖራትን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት፣ የማኅበራዊ፣ የሰላም እና የዲፕሎማሲ ግቦች እና መዳረሻዎችን እንጥራና ግልጽ ግብ አስቀምጣ እየተንቀሳቀሰች መኾኗንም ገልጸዋል፡፡
ጠንካራ የፖለቲካ መረጋጋት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ በዲፕሎማሲ በዓለም ተደማጭ የኾነች ሀገር ለመገንባት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተከማቹ ማነቆዎችን እና እዳዎችን አላቀን በመሻገር መዳረሻችን ላይ ግልጽ ግብ በማስቀመጥ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ግቦችን ለማሳካት በመጀመሪያ ደረጃ ተቋም መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በተቋም እና በፓርቲ ግንባታ ላይ በመመሥረት የምንፈልጋትን ሀገር ለዜጎቿ የተመቸች እንድትኾን አድርጎ ለመገንባት በግልጽ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡
ተቋም እንገባ ስንል መሪ፣ ሠራተኛ እና ተገልጋይ እንገባ ማለት ነው ብለዋል፡፡ ሀገር እንገባ ሲባል የማኀበረሰብን ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አለብን ነው ያሉት፡፡ የተቋም፣ የፓርቲና የሀገር ግንባታን ለማረጋገጥ ቀዳሚው መሪዎችን መገንባት መኾኑንም አንስተዋል፡፡
መሪን ሳንገነባ ሠራተኛን ልንገነባ አንችልም፣ መሪን ሳንገነባ ተገልጋይ ልናረካ አንችልም፣ መሪን ሳንገነባ ፓርቲ ልንገነባ አንችልም፣ መሪን ሳንገነባ ሀገር ልንገነባ አንችልም፣ መሪን ሳንገነባ መንግሥት ልንገነባ አንችልም ነው ያሉት፡፡ ዋናው ማዕከል መሪን መገንባት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በተለይም የፖለቲካ መሪነት የፖለቲካ አውዱ ከሚፈጥራቸው ብዥታዎች በየጊዜው ማላቀቅ፣ ግልጽነትን የፈጠረ፣ ራዕዩን የተገነዘበ፣ ለሕልሙ የሚተጋ መሪን መፍጠር ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ፓርቲው ለመሪነት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው በተግባር ላይ የተመሠረተ እና የንድፈ ሃሳብ ስልጠናዎችን በማደራጀት የመሪዎች አቅም ግንባታ ሲፈጠር መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡ ፓርቲው የተጠኑ እና የተዳራጁ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡ የተሰጡ ስልጠናዎች መሪዎች የተቀራረበ አመላከከት እንዲኖራቸው ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ማኅበራዊ እና ተፈጥሯዊ ማንነቶች እንደተጠበቁ ኾኖ የፓርቲው መሪዎች አንድ የሚያደርጋቸውን አስኳል ጉዳይ ለይተው እንዲንቀሳቀሱ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
አሁን የተጀመረው ስልጠናም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ሕልም ወይም ራዕይ መዳረሻን አውቆ ራስን ለማዘጋጀት ትልቅ መሳሪያ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ዓላማ እና ራዕይ ሳይኖረው የሚንቀሳቀስ መሪ ውጤቱ ባለበት መርገጥ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ራዕያችን አስቀምጠን፣ በአቅጣጫችን ላይ ግልጽ ኾነን መንቀሳቀስ ይገባናል ብለዋል፡፡ ስልጠናው ድክመቶቻችን እና ጥንካሬዎቻችን በመለየት የሕልማችን ተጋሪዎች እንድንኾን እና ሕልማችንን እውን የሚያደርጉ ኃይሎችን እንድናሰባስብ፣ በራሱ የነቃ እና የተደራጀ አመራር እና ማኅበረሰብ እንድንፈጥርን የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ሕልማችን ለማሳካት ዓይነታዊ ለውጥ በማምጣት መንቀሳቀስ አለብን ነው ያሉት፡፡ ብዙ ፈተናዎች አሉብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከግራ እና ከቀኝ ያሉ ጽንፈኛ አመለካከቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በፍጥነት መሻገር ግድ የሚሉ ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ችግሮችን አውቆ በፍጥነት መውጣት ይገባልም ብለዋል፡፡ አሁናዊ ሁኔታውን መገንዘብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ሁለንተናዊ ውጤታመነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም መስክ ውጤታማነትን የሚያሻሽል ሥራ መስራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ በማኅበረሰብ ቅቡልነት ያለው ሥነ ምግባር አዳብሮ መውጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የተሟላ ሥነ ምግባር ያለው መሪ መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ስኬታማ እንዲኾን አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች ትኩረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል፡፡ በስልጠናው ሰፊ ውይይት የሚደረግበት እና ግልጽ አቋም የሚያዝበት መኾን አለበትም ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!