የወልቃይት እና የራያ የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠራ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።

16

ባሕር ዳር: መስከረም 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክርቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በአንደኛ መደበኛ ሥብሠባው በስምንት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም የ2017 ዓ.ም የማንነት አሥተዳደር ወሰን እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዕቅዱን በዝግ ከመከረ በኋላ ለውሳኔ እና ውይይት ለምክር ቤቱ አቅርቦ በሙሉ ድምፅ አስጸድቋል። የምክር ቤት አባላትም ከተለመደው የዕቅድ አያያዝ ባለፈ በተግባር የማንነት ጉዳዮችን ለመመለስ ምን ምን እርምጃዎችን እንደሚወስድ ጠይቀዋል።

የማንነት አሥተዳደር ወሰን እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ፍቅሬ አማን የወልቃይት፣ የራያ እና የጠለምት የማንነት ጥያቄዎች በ2017 ዕቅድ መካተታቸውን በመጥቀስ የማንነት ጥያቄ በአንድ ዓመት የማይመለስ መሆኑን ጠቅሰው በሂደት ለመመለስ ይሠራል ብለዋል።
ከዚህ በፊት ሥራዎች የተጀመሩ ቢሆንም ባጋጠመው የፀጥታ ችግር መቋረጡን አንስተዋል፤ ወደፊትም አስቻይ ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ ለመፍታት በዕቅድ ይዞ መሥራቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ይህንን ለመፍታት ከትግራይ እና አማራ ክልሎች የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን በመጥቀስ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ይሠራል ብለዋል።
ቀጥሎም ተፈናቃዮችን በመመለስ እና የማስፈር ሥራ ከተሠራ በኋላ ሕዝበ ውሳኔ አንዲፈፀም አድርጎ ምላሽ ይሰጣል ሲሉ አብራርተዋል።

የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዋና ዓላማ የበይነ መንግሥታት ፊሲካል ሽግግሮች፣ የፌዴራል መሠረተ ልማት አውታሮች ስርጭት ፍትሐዊነት፣ ውጤታማነት ማረጋገጥ፣ የድጎማ እና የጋራ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዕቅድ ነው ተብሏል። ይህም በሙሉ ድምፅ ምክር ቤቱ ያፀደቀው ሲሆን የጋራ ገቢዎች ቀመር መሻሻሉን አፈ ጉባዔው ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በሕዝብ ቁጥር ብቻ ይሰጥ የነበረው ውስን ዓላማ ያላቸው የድጎማ በጀቶች በፍትሐዊነት ለክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ምክር ቤቱ ባፀደቀው አሠራር ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ አንዱ ተግባሬ ነው ያለው ምክር ቤቱ፣ የጋራ ገቢዎች አሠባሠብ አሥተዳደር እና ትልልፍ በተሻሻለው ቀመር መሠረት መፈፀማቸውን ማረጋገጥ ከተግባሮቹ መካካል እንደሚኾኑ አሳውቋል። በእነዚህ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአምባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ኾነው ተሾሙ፡፡
Next article“መሪን ሳንገነባ ሀገር ልንገነባ አንችልም” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ