
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቡ ወረዳ በረዶ እና ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ እና መሬት መንሸራተት 955 ሄክታር ማሳ በሸፈነ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገልጿል። የወረባቡ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም አሕመድ እንዳሉት በወረዳው ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም ፣ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም፣ ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም፣ ነሐሴ7/2016 ዓ.ም በረዶ እና ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ እና በመሬት መንሸራተት እንዲሁም በጎርፍ ጉዳት ደርሷል።
ጉዳቱ የደረሰው በወረዳው በሚገኙ 10 ቀበሌዎች ስለመኾኑ ነው የገለጹት፡፡ በዚህም ከ955 ሄክታር በላይ መሬት በተሸፈነ የማሽላ፣ የበቆሎ፣ የሰንዴ፣ የባቄላ እና ቋሚ አትክልቶች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ አስገንዝበዋል። በቢስቲማ ከተማ በደረሰው የመሬት መንሸራተትም 37 ቤቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት። በደረሰው ጉዳት 19 ሺህ 829 የቤተሰብ አባላት ለችግር መጋለጣቸውን ነው ያብራሩት።
የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለማልማት እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ የቋጠሩ ውኃማ አካባቢዎችን የማንጣፈፍ እና የማፋሰስ ሥራ እንዲሠራም ኀላፊው አሳስበዋል። አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!