
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ውብ ባሕል የኾነው የሻደይ በዓል በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ተመልምለው በመጡ የሻደይ ተጫዋቾች፣ ባሕሉን በሚያጎለብት እና ታሪኩን በሚመጥን አቀራረብ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት እተከበረ ነው፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈንታይቱ ካሴ የዘንድሮውን “የሻደይ በዓል ስናከብር በችግሮች ውስጥ ኾነን ስለኾነ በዓሉ ሰላምን በሚያመጣ እና ኢኮኖሚን በሚያነቃቃ መንገድ መከበር አለበት” ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ዋግ ኽምራ እና ሕዝቧ ውብ ባሕል እና አኩሪ ታሪክ ያለው መኾኑን አንስተው በተለይ አስደናቂው የሻደይ ባሕል የሕዝቡ ዋና መገለጫ እንደኾነ ተናግረዋል።
ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ የዘንድሮ በዓል ሌተናል ጄኔራል ኃይሉ ከበደን የሚስታውስ ቤተ መዘክር ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጥንበት በዓል በመኾኑ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!