
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለዘመናት የተጠበቀ ውበት፣ ለዘመናት የቆዬ እሴት፣ ለዘመናት ያልተናወጠ ማንነት፣ የጸና ሃይማኖት፡፡ ውበት ያለ ማቋረጥ እንደ ዥረት ይፈስሳል፣ ባሕል ሳይበረዝ ከልጅ ልጅ ይወራረሳል፡፡ እሴት ከእነ ክብሩ እንደ ካባ ይለበሳል፤ ባሕል ከእነሥርዓቱ ለትውልድ ይደርሳል፡፡
የዘመን ጌጦች፣ የታላቅነት ምሳሌዎች፣ የቀደምትነት አብነቶች፣ የታሪክ እና የባሕል አምባዎች፣ የፍቅር እና የሰላም መሶበወርቆች፣ የውበት ዥረቶች፣ የደም ግባት ምንጮች፣ የደስታ ውቅያኖሶች፣ የኩራት እና የክብር ተራራዎች፣ የተስፋ እና የተድላ ሰገነቶች ናቸው፡፡ ያያቸውን ያስቀናሉ፣ በአሻገር የተመለከታቸውን ያጓጓሉ፡፡ በደም ግባታቸው፣ በደግነታቸው፣ በመልካምነታቸው ቀልብን ይስባሉ፡፡
ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ያስተሳስራሉ። የጥንቱን መንገድ ሳይለቁ በቀጥተኛው መንገድ ይጓዛሉ፣ ከነበረው ሳይቀንሱ፣ ከሚመጣው ሳይጨምሩ፣ በልኩ እና በመልኩ ጠብቀው ይዘልቃሉ፡፡ የክብራቸውን መገለጫ አይለቁም፣ የማይመስላቸውን አይደባልቁም፤ በራሳቸው ኮርተው፣ በታሪካቸው እና በባሕላቸው ተመክተው ይኖራሉ እንጂ፡፡ ሃይማኖትን ባሕልን ማክበር ያውቁበታል፤ መጠበቅም ይችሉበታል፡፡ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እያሉ ለዘመናት በክብር ያኖሯቸዋል፡፡ ሕያው አድርገው ይጠብቋቸዋል፡፡ እነዚህ በዓላት በዋግ ኽምራ፣ በሰሜን ወሎ፣ በጎንደር ይከበራሉ፡፡
የባሕሎቻቸውን ነጻነትን፣ መልካምነትን፣ ደግነትን፣ ሰው አክባሪነትን፣ ታሪክ ጠባቂነትን፣ መከባበርን፣ አንድነትን፣ ፍቅርንና ደስታን ይሰብኩባቸዋል፡፡ ታሪክ ያስተምሩባቸዋል፡፡ የሀገርን ታላቅነት ይነግሩባቸዋል፡፡ ቀደምትነትን ይገልጡባቸዋል፡፡ የከበረ እሴት ባለቤትነትን ለዓለሙ ሁሉ ያሳዩባቸዋል፡፡
መነሻቸው ለሚወዷት እናታቸው፣ ለከበረች እመቤታቸው፣ ከአንደበታቸው ለማትለይ የጭንቅ ቀን መጠለያቸው፣ ቃል ለሚፈጽሙባት፣ በየንግግራቸው መካከል ስሟን እየጠሩ እውነትን ለሚገልጹባት፣ በጸሎታቸው ወቅት ለሚማጸኗት፣ በደስታም በመከራም አትርሽን ለሚሏት፣ በምድር ኾነው በሰማይ ለሚያስቧት፣ ከክብሯ ዙፋን ሥር ለመቀመጥ ለሚያልሟት እመቤት ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በመስጠት፣ እየሰገዱ ምስጋናን በማቅረብ ነው፡፡ በእርሷ ምክንያት ነጻነትን፣ በእርሷ ምክንያት ክብርን፣ በእርሷ ምክንያት ደስታን ያገኙ ዘንድ ያምናሉና ነጻነታቸውን ያውጃሉ፡፡ ሃይማኖቱን እና ባሕልን ጠብቀው ይይዛሉ፡፡
የፍልሰታ ጾም ስትጠናቀቅ፣ የማርያም ዕረገት ሲታሰብ ወይዛዝርት አምረው ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለልን እያዜሙ ይወጣሉ፡፡ ጎበዛዝቱ ደግሞ ተውበው ወይዛዝርቱን ይጠብቃሉ፡፡ ይህ ከጥንት ጀምሮ የመጣ ነው፡፡
የሻደይ በዓል አክባሪዋ ካሳነሽ ሞገስ የሻደይ በዓል ዓመት ጠብቆ እስኪመጣ ድረስ ይናፍቀናል፤ ጊዜ ይረዝምብናል ትላለች፡፡ ስለ ሻደይ አከባበር ስትነግረኝ በነሐሴ 16 ዋዜማ ማታ ሻደይ እናመጣለን፣ ያመጣነውን ሻደይ እንዳይደርቅ ከጤዛው እናሳድረዋለን፣ በ16 ማለዳ ባሕሉን የጠበቀ ጌጥ እናጌጣለን፣ አምረን እንዋባለን፣ ከዚያ በኋላም ወደ ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፣ በቤተክርስቲያንም እናረፍዳለን ብላለች፡፡
የቤተክርስቲያኑ ሥርዓት ካለቀ በኋላ “አስገባኝ በረኛ…” እያለን እያዘሜን በየመንደሩ እንዞራለን፣ በአባቶች እና በእናቶች እንመረቃለን፣ ይህ አከባበር ለሳምንት ይዘልቃል ነው ያለችኝ፡፡ በየመንደሩ የሚሰጠንን ገንዘብ ለታቦት እንሰጣለን ትላለች፡፡ ከሰባት ዓመት ሕጻናት ጀምሮ በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ነሐሴ 16 ተመልሶ እስኪደርስ ድረስ የማይቸኩል እና የማይናፍቅ የለም ነው የምትለው፡፡ በየመንደሮች እየተዘዋወሩ ሻደይ ሲሉ ስንኝ እየቋጠሩ ያዜማሉ፡፡ ካሳነሽ ስንኞቹን ስታስታውሰኝ እንዲህ ትላለች፡
ከፈረስ አፍንጫ ይገባል ትንኝ
እሰይ የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ፡፡
ይሄው እዚያ ማዶ የወስኮ ስባሪ
እሰይ የኔ ጌታ ንጉሥ አሳደሪ
ማሳደሩንማ ሁሉ ያሳድራል
እሰይ የኔ ጌታ ፍሪዳ ይጥላል
እኩል ከአንቱ ጋራ ማን ይስተካከላል፡፡
ከዱር አውሬ ሁሉ ሚዲያቋ ናት ጮሌ
እሰይ የኔ እመቤት አንገቴ ብርሌ፡፡
እሰይ የኔ ጌታ ጌትዬ ጌትዬ
አንቱ በበቅሎ ላይ እኔ ጠጅ አዝዬ፡፡
መሬት ጭሬ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ
እሰይ የኔ እመቤት የልቤ ወይዘሮ…። እየተባለ ሻደይ ይዜማል፡፡ በዓሉ ባለቀ ጊዜ ስንለያይ ከዓመት እስከ ዓመት በቸር አድርሰን፣ አትለየን እያለን እንማጸናለን ትላለች፡፡ ዓመት ደርሶ ዳግም እስክንገኛኝ ሻደይን እስክናብር እየተነፋፈቅን እንለያያለን፣ ሻደይ ፍቅር፣ ደስታ፣ ተስፋ ያለበት ነውና ነው የምትለው፡፡ ሻደይ በዋግ ኸምራ በድምቀት የሚከበር፣ ጥንታዊ በዓል ነው፡፡
ከሻደይ ባለፈ አሸንድዬ እና ሶለልም ከነሐሴ 16 ጀምረው በሌሎች አካባቢዎች በድምቀት ይከበራሉ፡፡ ስለ አሸንድዬና ሶለል ደግሞ የነገሩን የሰሜን ወሎ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ገነት ሙሉጌታ ናቸው፡፡ አሸንድዬ እና ሶለል ከነሐሴ 16 እስከ 21 ድረስ በድምቀት ይከበራሉ ይላሉ፡፡ አሸንድዬ በላስታ፣ በግዳን፣ በመቄት፣ በቡግና፣ ዋድላ፣ ዳውንት እና አንጎት ይከበራል፡፡ አሸንድዬ ሲከበር ልጃገረዶች የሚዋቡበት፣ ነጻነታቸውን የሚያውጁበት፣ የነጻነታቸው ቀን ነው፡፡
አሸንድዬ ሃይማኖታዊም ባሕላዊም ነው፡፡ መነሻው ከሃይማኖት እና ከባሕል ጋር የተቆራኘ ምስጢር ያለው በዓል ነው ይሉታል፡፡ ሶለል በራያ፣ በሀብሩ፣ በጉባ ላፍቶ፣ በጋዞ በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት፡፡ አሸንድዬ እና ሶለል ሴቶች የእኩልነት መብታቸውን የሚያረጋግጡበት ነው ይላሉ፡፡ ልጃገረዶች በዓሉን ሲያከብሩ መነሻቸው ከቤተክርስቲያን ነው፣ በቤተክርስቲያን ሄደው ሰግደው፣ በአባቶች ተባርከው እና ጸሎት ተደርሶላቸው ይወጣሉ፡፡ ከተባረኩ በኋላ አሸንድዬ እና ሶለል እያሉ በየመንደሮች ይዘዋወራሉ፡፡ ከአበው እና ከእመው እየተመረቁ፣ ከዓመት ዓመት እንዲያደርሳቸው እየተመኙ ይጫወታሉ፡፡
አሸንድዬ እና ሶለል ማንነት፣ ሃይማኖት፣ የሀገር ታላቅነት የሚገለጥባቸው ናቸው ይሏቸዋል፡፡ በዓላቱ ሳይበረዙ እናቶች ለልጆቻቸው እያስረከቧቸው እዚህ ዘመን የመጡ ናቸው፡፡ በአሸንድዬ እና ሶለል ውበት እና ጸጋ ይታያል፤ የማንነት እና ሃይማኖት መገለጫዎች ናቸው፡፡ አሸንድዬ እና ሶለል ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በመኾናቸው እነርሱን አለማክበር አይቻልም ነው የሚሉት፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በዓላቱ የክልሉ ድንቅ ሃብቶች ናቸው ይሏቸዋል፡፡ በሰፊ አካባቢዎች የሚከበሩት በዓላቱ ኩራት እና ማንነት ናቸው፡፡ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላቱ አንድነት የሚገለጽባቸው፣ የሕዝብ አብሮነት የሚነገርባቸው ናቸው፡፡ እሴት እና ባሕል የሚጠበቅባቸውም ውብ በዓላት ናቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!