
አዲስ አበባ: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ሀገር ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት በሚካሄደው የአንድ ጀምበር 600 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር 317 ሺህ 521 ሄክታር መሬት ለተከላ ዝግጁ መደረጉ ነው የተገለጸው።
አፋር ክልልም ለአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ርእሰ መሥተዳደር ሐጂ አወል አርባ አስታውቀዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ክልል ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። ነገ በሚከናወነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም ማኅበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ነገ ለሚከናወነው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በ192 ሳይቶች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞች እንደተዘጋጁ የተናገሩት የአፋር ክልል የግብርና ቢሮ ኀላፊ ሐጅ ኢብራሂም ኡስማን ለዚህም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጉድጎዶች ተዘጋጅተዋል ብለዋል። ለእነዚህ ችግኞችም 1ሺህ 200 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላው ከ200ሺህ በላይ ሕዝብ እንደሚሳተፍም ቢሮ ኀላፊው ለአሚኮ ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ሥራው ባለፉት አምስት ዓመታት አፋር ክልል ላይ ለውጥ አምጥቷል ያሉት የግብርና ቢሮ ኀላፊው ሐጂ ኢብራሂም በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለአጎራባች ክልሎችም እየላኩ ስለመኾኑ አስረድተዋል፡፡ የችግኝ ተከላው የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንዳስቻለ ነው የገለጹት፡፡ ማኅበረሰቡ ከዓመት ዓመት ግንዛቤው በማደጉ ችግኝ ከመትከል ባለፈ መንከባከቡ ላይም እያገዘ ስለመኾኑም አረጋግጠዋል።
በተያዘው የክረምት ወር እንደ ክልል 10 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተሠራ ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው ከእነዚህ ውስጥም 60 በመቶ የሚኾኑት ለምግብነት የሚውሉ መኾናቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በተያዘው ክረምት 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ እየተንቀሳቀሰች መኾኑን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዐቢይ ኮሚቴ ማሳወቁ ይታወሳል።
ባለፉት አምስት ዓመታትም 32 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፤ እስከ 2018 ደግሞ 50 ቢሊዮን ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑንም የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። አሁን እየታየ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እስከ 2030 የደን ሽፋኗን 30 በመቶ እንደሚያደርስም መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!