
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቻይናው አሊባባ ግሩፕ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማኀበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የኢኮሜርስ ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ያደረገበት መድረክ ተካሄዷል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ.ር) የአሊባባ አሊ ኤክስፕረስ በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩ ዓለም አቀፋዊ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ እንዲሁም ለዲጂታል ፈጠራ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መኾናቸውን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ድርጅቱ የሚያቀርባቸው የዲጂታል መሣሪያዎች እና አማራጮችን በመጠቀም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ተዋናይ ለመኾን ያላትን አቅም እና ዝግጁነት ማሳየት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ አያሌው አየር መንገዱ አሊባባ ግሩፕ በኢትዮጵያ የሚጀምረውን የኢኮሜርስ ሥራ ለማሳለጥ የሚያስችል የኢኮሜርስ ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚሰጥ ማዕከል (ሀብ) ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የአሊ ኤክስፕረስ ቢዝነስ ዳይሬክተር ጄፍሪ ጂያንግ “አሊ ኤክስፕረስ በኢኮሜርስ ያለውን ዓለም አቀፍ ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያውያን ሸማቾች እና የንግድ ቦታዎችን እንቅስቃሴ ለማሥተሳሰር ይሠራል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማኀበር ፕሬዝዳንት ፍቅር አንዳርጋቸው ማኀበሩ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እንቅስቃሴ ውጤታማነት ለማገዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።
ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማኀበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የማኀበሩ ፕሬዝዳንት ፍቅር አንዳርጋቸው እንደ አሊባባ ያሉ የኢኮሜርስ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀላቸው የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!