
ሁመራ: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፍልሰታ ጾም መግባትን ተከትሎ የኦርቶዶክ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች በአንድነት በመሠባሠብ ያላቸውን በመካፈል “ዓመት ከዓመት አይለያየን፤ ዓመት እንደ ዕለት ያድርሰን” እያሉ ቆሎ እና ጠላ በማዘጋጀት “አድርሽኝ” ይጠጣሉ። ጎንደር “አድርሽኝ” በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል። አድርሽኝ ከጾሙም በኋላ በማኅበሩ ውስጥ ያለው ሰው ከፍሎ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሊቀጥል የሚችል ሕዝብን የሚያገናኝ የሕዝብ ማኅበራዊ እሴት ነው፡፡
የጎንደር አንዱ ክፍል የኾነው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብም ከአባቶቹ የወረሰውን “የአድርሽኝ” ሥርዓት በማስቀጠል ላለፉት ዘመናት አድርሽኝን በአንድነት እና በፍቅር ሲያከናውን ቆይቷል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አዳነች አለበል የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ባሕል እና ትውፊቱ ከጎንደር አማራ ሕዝብ ጋር የተቆራኘ መኾኑን አንስተዋል።
የዞኑ ሕዝብ ባለፉት ዘመናት የአድርሽኝ ሥርዓትን በአንድነት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው አካባቢው በኀይል ለሦስት አሥርት ዓመታት ባሕሉን እንዲያጣ የአድርሽኝ ሥርዓትን እንዳያከናውን እስር እና እንግልት ይደርስበት እንደነበር አስታውሰዋል። የአካባቢው ሕዝብ አድርሽኝን በአንድነት በመጠራራት የተቸገረን የሚረዳበት፤ የተጣላን የሚያስታርቅበት፤ ደስታ እና ሀዘንን የሚካፈልበት እና በኀይል የተነጠቀ ማንነቱን ለማስመለስ የሚወያይበት በመኾኑ በአድርሽኝ ሥርዓት እንዳይሠበሠብ ጫና ይደርስበት እንደነበር ገልጸዋል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ባሕሉን አስጠብቆ ለመዝለቅ መስዋዕትነት መክፈሉን አስታውሰው ከነጻነት ማግስት የአድርሽኝ ሥርዓቱን ጨምሮ ሌሎች የማኅበረሰቡን ባሕል እና ትውፊት ለማስጠበቅ ይበልጥ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የአድርሽኝ በዓል የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ የበጌምድር አማራዊ መገለጫው ነው ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ናቸው።
በሕወሓት አስከፊ የግዛት ዘመን ማኅበረሰቡ ባሕል እና ትውፊቱን እንዳያስቀጥል እስከ መከልከል ቢሞክርም በሕዝቡ የእምቢተኝነት ትግል እያከበረ ለትውልዱ እያወረሰ መጥቷል ብለዋል። አድርሽኝ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የሕዝቡ ባሕል እና ትውፊት የሚተላለፍበት አብሮነት እና መረዳዳት የሚጎለብትበት እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!