
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክረምቱ አልፎ አዲስ ዓመት የተስፋ ዘመን ይዞ መምጣቱ የሚበሰርበት የደስታ፣ የጭፈራ እና የምስጋና በዓል ነው – ሶለል፣ ሻደይ እና አሸንድየ፡፡ በክርሥትና ሃይማኖት ሥርዓት የፍልሰታ ጾም ማብቃትን ተከትሎ መከበር ለሚጀምረው ሶለል በዓል ሕጻናት እና ልጃገረዶች ልብሶቻቸውን ማደራጀት፣ መዋቢያ እቃዎቻቸውን ማዘገጃጀት፣ አሸንዳ መቁረጥ ብሎም የጭፈራቸውን ግጥም እና ዜማ መለማመድ ይጀምራሉ፡፡
በራያ ቆቦ የሶለል ዓመታዊ እና ባሕላዊ ክዋኔ ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች በባሕላዊ ልብሶቻቸው ተውበው ከጓደኞቻቸው ጋር የሚዘልሉበት እና የሚቦርቁበት፣ በሕብረ ዜማ እና ጭፈራ ለታላላቆች የእንኳን አደረሳችሁ እና የመልካም ምኞት መልዕክት የሚያቀርቡበት፣ በምላሹም ምርቃት እና ስጦታ የሚቀበሉበት ደማቅ በዓል ነው፡፡
የራያ ልጃገረዶች እንደ እድሜያቸው እና ማግባት አለማግባታቸው ሁኔታ በተለያየ አለባበስ እና ጌጣጌጥ ተውበው የሚታዩበት ነው – የሶለል በዓል፡፡ “ማይማዮ” የሚባል የሸማ ቀሚስ ለብሰው፣ በበዓሉ ዋዜማ ጎንጉነው ያዘጋጁትን አሸንድየ ታጥቀው፣ ተፈጥሮ ካደለቻቸው ድንቅ ውበት ላይ የተለያዩ ጌጣጌጦችን አድርገው፣ በፍልቅልቅ ገጽታ እና በማራኪ ዕይታ በለምለሙ ሜዳ ሲቦርቁበት ያየ ሰው ፈጣሪም ለዚያ አካባቢ ውበት እንዳዳላ ይገምታል።
በበዓሉ በእኩያነታቸው ከሚሰባሰቡት ልጃገረዶች መካከል የቡድኑ መሪ ትመረጣለች፡፡ በቅድሚያ እያዜሙ ከአጥቢያው ቤተክርስቲያን ከተሳለሙ እና እጅ ከነሱ በኋላ በየቤቱ እየዞሩ የእንኳን አደረሳችሁ እና የመልካም ምኞት ዜማ ማቅረብ ይጀምራሉ፡፡ እንደየአባዎራ እና እማዎራዎቹ ሁኔታም ያወድሳሉ፡፡
በቡድን ኾነው ወደ እማዎራ እና አባዎራዎቹ ቤት ሲደርሱ፡-
ሶለለለለል…. ሶለለለል…..
ሶለለለል … ይሄ የማነው ቤት…
ሶለለለል የኮራ የደራ…
ሶለለለል… እስከ ባለቤቱ…
ሶለለለል… ስሙ የተጠራ…
ሶለለለለል…. ከፈረስ አፍንጫ…
ሶለለለለል…. ይውላል ትንኝ…
ሶለለለለል…. የዚህ ቤት ባለቤት…
ሶለለለለል…. ጤና ይስጥልኝ፡፡
በማለት በጋራ ውዝዋዜ ካዜሙ በኋላ በከበሮና ጭብጨባ በታጀበ ፈጣን ስልተ ምት፡-
አቀንቃኟ፡-
አሸንድየ… ብላ ማቀንቀን ስትጀምር ጓደኞቿ እያጨበጨቡ
እሆ…. በማለት ይቀበሏታል፤
አሸንድየ…
እሆ….
አሸንዳ ሆይ…
እርግፍግፍ አትይም ወይ፡፡
አሸንድየ…
እሆ…
አሸንዳ ሙሴ
እርግፍግፍ እንደ ቀሚሴ፡፡
እርግብየ….
እሆ ……
እርግብ ለማዳ
ወረደች በራያ ሜዳ፡፡
እርግብየ…
እሆ…
እርግብ ለሰሴ…
ወረደች በራያ ደሴ፡፡
ሎሚ ወድቃ
እህ……
ኋላየ ላየ….
ኧረ አንሻት ባልንጀራየ፡፡
አበባየ…
እሆ…
ኧረ አበባየ…
አበባ… እሽ አበባየ
አበባ… እሽ አበባየ…. እያሉ በሞቀ ጭብጨባ እና ድምጸት፣ በእልልታ ወደላይ በመዝለል የዙሩን ጭፈራ ያሳርጋሉ፡፡ ከዚያም ደስ ወዳላቸው ወደሌላኛው ዜማ፣ ጭፈራ እና ስልተ ምት ይገባሉ፡፡
ከሕብረ ዝማሬያቸው እና ጭፈራቸው በኋላም ከአባዎራ እና እማዎራዎቹ ምርቃት እና ስጦታ ይቀበላሉ፡፡ ስጦታው ዳቦ፣ የምግብ ዱቄት ወይም ገንዘብ ሊኾን ይችላል፡፡ ሁሉም የቻለውን እና የፈቀደውን ይሰጣል፣ ልጃገረዶቹም ይቀበላሉ፣ ለስጦታውም በዜማ ያመሰግናሉ፡፡
ከብረው ይቆዩን ከብረው፣
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው፣
ሰላሳ ጥጆች አስረው፣
ከብረው ይቆዩን ከብረው፣
ከብረው ይቆዩን ከብረው…፡፡
በማለት አመስግነው ወደሌላኛው ቤት ይሄዳሉ፡፡
ሶለል ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ ቢኾንም በዋናነት የልጃገረዶች በዓል እና ክዋኔ ነው፡፡ ወጣት ወንዶችም ልጃገረዶችን በማጀብ ዝማሬ እና ጭፈራቸውን በማዳመጥ የትዳር አጋር የምትኾናቸውን የሚፈልጉበት እና የሚመርጡበት ዓመታዊ የዜማ፣ የጭፈራ፣ የውበት ማሳያ እና የመተጫጫ ድግስ ነው፡፡
ክምክም ጎፈሬያቸው ላይ ሚዷቸውን ሻጥ አድርገው፣ ሸሚዝ እና ሱሪን በሚተካ ከሸማ የተሠራ “እርቦ” እና “ጎምቢሶ” በሚባል ልብስ አጊጠው፣ የሽንጥን ርዝመት በሚያጎላ “ዲግ” የተሰኘ መታጠቂያ ጠምጥመው፣ “ጥርቅ” የሚባል ባሕላዊ ጫማ ተጫምተው፣ አንድ እግራቸውን በሌላኛው እግራቸው ላይ አነብባብረው እና “መዋጣ” የሚባል ዱላቸውን ተመርኩዘው፣ ጥርሳቸውን እየፋቁ በኩራት አግድመው ወደ ልጃገረዶቹ ይመለከታሉ፣ ከፈለጉም ልጃገረዶቹን ይከተላሉ፡፡
ወጣቶቹ እንደ በቆሎ እሸት የተደረደረ እና የነጣ ጥርሳቸውን “ሲዋቅ” ከሚባል ዛፍ በተዘጋጀ የጥርስ መፋቂያ ሲፍቁ ላያቸው ነጭ ጥርሳቸውን ለማንጣት ሳይኾን ፍቆ ለመጨረስ የሚታገሉ ይመስላሉ፡፡ በአጠቃላይ ራያዎች ሶለልን ሲያከብሩ ብቻ ሳይኾን በአዘቦትም አለባበሳቸው፣ ንጽህና መጠበቂያቸው፣ ጌጦቻቸው፣ ትጥቆቻቸው እና መስተጋብራቸው ሳይቀር ባሕሉን የጠበቀ ነው፡፡
ልጃገረዶች እና ህጻናት ሴቶች በየቡድናቸው ኾነው በሜዳ ላይ ሲጨፍሩ ወጣት ወንዶችም በቡድን በቡድን ቆመው ይመለከታሉ፣ ወይም ይከተላሉ፡፡ ያላገባ ወጣት ቀልቡን የሳበችውን ኮረዳ ወገቧ ላይ ካሰረችው አሸንድየ በመምዘዝ ወይም ሌላ አማራጭ ዘዴ በመፈለግ የ”ፈልጌሻሁ” መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡ ኮረዳዋም በጨረፍታ ዐይታ በፍቅር ጥያቄው ላይ መስማማት አለመስማማቷን በመሽኮርመም ወይ ፊቷን በማኮሳተር ምላሽ ትሰጣለች፡፡ ኮበሌው መስማማቷን ከተረዳም ወላጆቹ እንዲያጩለት ይጠይቃል፡፡
ይህ ዓመታዊ እና ለቀናት የሚቆይ በዓል ልጃገረዶች የሚተውኑበት፣ ወጣቶች እና ህጻናት የሚያጅቡት እና የሚያደምቁት የደስታ በዓል ነው፡፡ ጎልማሶች እና ሽማግሌዎች የባሕሉ እርሾ ኾነው፣ በሃሳብ፣ በገንዘብ እና በቁሳቁስ እያገዙ፣ እየመረቁ እና እየመከሩ ያሳለፉትን ጊዜ በዓይነ ህሌናቸው እያስታወሱ በናፍቆት እና በትዝታ ጭል…ጥ የሚሉበት፤ ሲነሽጣቸውም ወደ ጭፈራው ገብተው አንገት እና ትከሻቸውን የሚፈትሹበት እና የሚሰብቁበት ባሕላዊ መድረክ ነው፡፡
ሶለል የራያዎች ሙዳይ ሲከፈት ከሚገኙ ቀደምት እና ውብ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት እና የሰላም ስንቅ ከኾኑ የማንነት መገለጫ ባሕላዊ እሴቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡
የሶለል ባሕላዊ እሴትን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት ቁንጅና እና ውበታቸውንም በሚታይ እና በሚዳሰስ፣ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ እሴት ማስመዝገብ ተገቢ ነው፡፡
የራያን ህጻናት፣ የልጃገረዶቹንም ኾነ የወንዶቹን ውበት፣ እርጋታ እና ለዛ፣ ፍቅር እና መከባበር፣ ፈገግታ እና ትህትና ላስተዋለ፡-
ትህትና በድምቀት ፈገግታ በጸዳል
እርጋታ በለዛ ፍቅር በልዝብ ቃል
ተስፋ በተመስጦ በአርምሞ ቢለካ
ውበት ግኡዝ ኾኖ ይዳሰሳል ለካ… ማለቱ አይቀርም
ተነግሮ በማያልቅ፣ በፍጹም ልባዊ ፍቅር እና ደስታ የሚከበረው የሶለል በዓል፣ በአብዛኛው ነሐሴ 16 እና 17 በየቤቱ፣ በየመንደሩ እና በየሜዳው በድምቀት ተከብሮ፣ ኮበሌ እና ኮረዳን አስተያይቶ፣ አከጃጅሎ እና ለተከበረ ትዳር አድርሶ፣ የደስታ ስሜቱን በየልጃገረዶቹ እና ወጣቶቹ ልብ አንግሦ፣ ለቀናት እየተዜመ እና እየተንጎረጎረ፣ ለአዲስ ዓመት መቀበያው- ለእንቁጣጣሽ በዓል ያስረክባል፡፡
በሶለል ባሕል ላይ አንድ አደጋ ብቅ ያለ ይመስላል- የመበረዝ አደጋ፡፡ ሶለል እንደሌሎች ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሰው ሠራሽ ቅርሶቻችን ሁሉ ለአደጋዎች ተጋልጧል፡፡ ምን ዓይነት አደጋ የተባለ እንደኾን ከራሱ ባሕል እና ታሪክ ይልቅ በውጪ ባሕል እና ልምድ በተበረዘ ትውልድ ዘመን ሶለልን የሚጫወቱት እና የሚያከብሩት ልጃገረዶች ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው፡፡ የልጃገረዶች ሶለልን መመልከት እንጂ መጫዎት እየቀነሰ ነው ይላሉ እናቶች እና አባቶች፡፡
የኢትየጵያ ባሕል፣ ታሪክ እና ማንነት ያልኾነ አለባበስ እና አጊያጊያጥ፣ ጭፈራ እና ግጥምም በሂደት ባሕሉን እየበረዘው ሲኾን፣ በዓሉን ለማክበር የሚሰባሰቡ ልጀገረዶች እና ህጻናትም ትኩረታቸው ገንዘብ መለመን እና መሰብሰብ ላይ መኾኑም ሌላኛው የባሕሉ ስጋት ነው፡፡
ባሕላዊ እሴቱን በጥናት እና ምርምር እያዳበረ የሚዘልቅ ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩ በመጪው ጊዜ ባሕሉ ተረስቶ ወይም በሌሎች ባዕድ ባሕሎች ተበርዞ ትክክለኛ የሕዝብ እሴትነቱን እንዳያጣ ብሎም እንዳይጠፋ ሕዝቡ እና መንግሥት ከወዲሁ ጥበቃ እና አንክብካቤ ሊደርጉለት ይገባል፡፡
መልካም የሶለል፣ ሻደይና አሸንድየ በዓል!!!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!