
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እያከናወነ ባለው አጀንዳ የማሠባሠብ ተግባር የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ባለድርሻ አካላቱ በተወካዮቻቸው አማካኝነት በሂደቱ ላይ ተሳታፊዎች በመኾን ላይ እንደሚገኙም ተብራርቷል፡፡ በውይይት እና በምክክር የዳበሩ አጃንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ እያቀረቡ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ ሂደት ላይ ተሳታፊ እንዲኾኑ ከለያቸው ባለድርሻ አካላት መካከል፡-
✍️ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው ከየወረዳው የተመረጡ ተወካዮች
✍️መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት እና የማኅበራት ተወካዮች
✍️የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ተወካዮች
✍️ከሦሥቱ የመንግሥት አካላት የተውጣጡ የተቋማት ተወካዮች
✍️ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር፣ በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በሐረሪ ክልል እና በጋምቤላ ክልል በባለድርሻ አካላት ወኪሎች አጀንዳዎችን በተሳካ ሁኔታ ስለማሠባሠቡም ነው የተብራራው፡፡
በቀጣይም በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተመሳሳይ ተግባራት እንደሚከናወን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!