በ2017 በጀት ዓመት 200 ሺህ የሚጠጉ ወጣቶችን በኮደርስ ኦንላይን ሥልጠና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ፡፡

18

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኮደርስ ኦንላይን ሥልጠና አተገባበር ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ በአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አማካኝነት በተዘጋጀው ውይይት የክልል ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኅላፊዎች እና የአይሲቲ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የካቢኒዎች ጉዳይ ኅላፊ ዳንኤል ደሳለኝ ዓለም ዲጂታላይዝ እየኾነች ስለኾነ እኛም ከዚህ የዲጂታል ዓለም ውስጥ መቀላቀል ግድ ይለናል ብለዋል።

እንደ ኅላፊው ገለጻም በአማራ ክልል የኢትዮ ኮደርስ የኦንላይን ሥልጠና ለመውሰድ የተመዘገቡት ወጣቶች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው። በመኾኑም የሕዝብ ግንኙነት እና የአይሲቲ ባለሙያዎች ስለጉዳዩ ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች በማካፈል ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሥራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ምክትል ኅላፊ አማረ ዓለሙ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለሀገር ዕድገት እና ለወጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል። ወቅቱ የዲጂታል ዘመን በመኾኑ በዲጂታል የታገዙ ተቋማትን፣ መሪዎችን እና ማኀበረሰብን መፍጠር ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት በሦሥት ዓመታት እና በሦሥት ዙሮች ለ5 ሚሊዮን ወጣቶች የኮደርስ ኦንላይን ሥልጠና ለመስጠት ወደ ሥራ መግባቱን አቶ አማረ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በሦሥት ዓመታት ውስጥ 767 ሺህ 963 ወጣቶችን ለማሠልጠን መታቀዱን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኅላፊው በ2017 ዓ.ም ደግሞ 191 ሺህ 991 የሚጠጉ ወጣቶችን የሥልጠናው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሥልጠናውም በሁሉም የክልል ተቋማት ተደራሽ እንደሚኾን ነው የተናገሩት።

ሥልጠናው የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ነው ያሉት ኅላፊው በሌሎች ሀገራት ሁሉን አቀፍ ሥራዎች እና ትምህርት ውስጥ ተሳታፊ ለመኾንም የኮደርስ ኦንላይን ሥልጠና አስፈላጊ ነው ብለዋል አቶ አማረ።

የአማራ ክልል በየወቅቱ በሚፈጠር የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የጸጥታ ችግር ምክንያት በዲጂታላይዜሽን ልማት ረገድ ከሌሎች ክልሎች ያነሰ ተሳትፎ እንዳለው የጠቆሙት አቶ አማረ “የክልላችን ወጣቶች ተገቢውን የዲጂታል ክህሎት ካላገኙ ከሌሎች ሀገራት እና አካባቢ ወጣቶች ጋር ተወዳዳሪ መኾን አይችሉም” ብለዋል።

አቶ አማረ እንደገለጹት ወጣቶች በገበያ ውስጥ ገብተው ለመወዳደር ሥልጠናው በእጅጉ አስፈላጊ በመኾኑ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ከሕዝብ ግንኙነት ኅላፊዎች እና አይሲቲ ባለሙያዎች ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም ሥልጠናው ለወጣቶች በርካታ ዕድሎችን ይዞ የመጣ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ለሀገራችን የእድገት ጉዞ ወሳኝ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለሻደይ፣ አሸንድየና ሶለል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።