
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ ታሪክ በዋግ እና በላስታ፤ በራያ እና ቆቦ አካባቢ የበዓሉ ታሪካዊ አጀማመር በማስመልከት በቀሳውስት ዘንድ በስፋት የሚነገርለት በዓል ነው፡፡ ታሪኩም ከድንግል ማርያም ገድላት ጋር የተያያዘ እንደኾነ ይወሳል፡፡ የሻደይ በዓል የሚከበረው የፍልሰታ ፆም መፈታትን ምክንያት በማድረግ ሲኾን “ፍልሰታ” የሚለው ቃል ደግሞ አጸደ ተፈራ (ዶ.ር) በ2ዐዐዐ ዓ.ም የሻደይ መጽሄት ላይ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጠቅሰው እንዳሰፈሩት “የቅድስት ድንግል ማርያም ስጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን ኋላም በገነት በእፀ ሕይዎት ስር ከነበረበት መነሳቱን” የሚያመላክት ቃል ነው፡፡
“ፍልሰታ” የሚለው የግእዝ ቃልም በአማርኛ ቋንቋ ቀጥታ “መፍለሷ” የሚለውን ቃል የሚወክል ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ የቤተክርስቲያን አባቶች የሻደይ በዓልን አጀማመር ከእመቤታችን ጋር አያይዘው ከመጥቀሳቸው ባሻገር፣ በዓሉ በአመዛኙ በልጃገረዶች ብቻ የሚዘወተር መኾኑ በራሱ ከእመቤታችን ጋር ተዛማጅነት እንዳለው ሌላ ማሳያ ነው፡፡
የቀድሞው የዋግ ኽምራ ሀገረስብከት የስብከት ወንጌል መምሪያ ኀላፊ የነበሩት መጋቤ ምስጢር ገብረሕይዎት ኪዳነማርያም ይህንን አስመልክተው የተናገሩት “በዓሉ በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የኾነው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመክፈቱ ነው” ካሉ በኋላ በዚህም መመኪያቸው ስለኾነች ልጃገረዶች በዓሉን ያከብሩታል፡፡ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት በእርሷ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
እኝህ አባት በሌላ አቅጣጫ የሻደይ በዓልን የኖህ ዘመን ልምላሜ ተምሳሌት አድርገው የሚወስዱ አባቶች እንዳሉ ጠቅሰው ድንግል ማርያምም በኖህ መርከብ እንደምትመሰል አስረድተዋል፡፡ ተምሳሌቱንም ሲያብራሩ “የሰው ልጅ በኖህ መርከብ ከጥፋት እንደዳነ ሁሉ በልጇ ያመኑና በእርሷ የአምላክ እናትነት የተማጸኑ ሁሉ ይድናሉ፡፡ በዚህም በኖህ መርከብ ትመሰላለች” ብለዋል፡፡
የሻደይ ቅጠል የኖህ ርግብ ያመጣችው የለመለመ ቅጠል ተምሳሌት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ልጃ ገረዶች ቅጠሉን እያሽከረከሩ መጫወታቸው ወይም መሽከርከሩ ደግሞ እያሸበሸቡ ድንግል ማርያምን ያሳረጓትን መልዓክትን ይዘክራል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ሁለት አተራሪኮች የሻደይ በዓል አከባበር ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋርም ይኹን ከኖህ መርከብ ጋር ተዛማጅነት እንዳለው መመልከት ይቻላል፡፡
በእነዚህ መረጃዎች መሠረት የሻደይ በዓል የሚከበረው ከክርስትና ሃይማኖት መጀመር በኋላ በቅድስት ድንግል ማርያም እርገት አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ባሕል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከሚገኙ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ መስህቦች ውስጥ አንዱ እና በወርሐ ፆመ ፍልሰታ ሁል ጊዜ በየዓመቱ በ16ኛው ቀን በድምቀት የሚከበረው የሻደይ በዓል ጨዋታ ነው፡፡
ሃዋሪያት ቅድሳን አንዕስት፣ ደናግል፣ ፃድቃንም የቅድስት ድንግል ማርያም የእርገት በዓሏን በየአድባራቱ ነሐሴ 16 ቀን በየዓመቱ በዝማሬ እና በእልልታ በተመሳሳይ ያከብሩት እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡ ይህም በተዋረድ ትስስር እና ትልቅ ታሪክ ባለው ሃይማኖታዊን በዓል ምዕመኑ ተቀብሎ በነጫጭ አልባሳት እና ጌጣጌጥ እንዲሁም ለማሸብሸብ እንዲያመች ሴቶች የሻደይ ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር እንሆ ሻደይ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
ሻደይን በሀገር ውስጥ በተመረቱ አልባሳት እና ጌጣጌጦችን በመልበስ ማክበር እንደ ግለሰብ አዋቂነት እንደ ቡድን ክብር እና ኩራት ነው፡፡ ባሕላችን የማንነታችን መገለጫ ነው የምንለው ሌላ በውጭ ሀገር የተፈበረኩ ባዕድ ነገሮችን ሳናቀላቅል በሀገር ውስጥ የተመረቱ አልባሳትን እና ጌጣጌጦችን ስንለብስ ነው፡፡
በእዚህ ዙሪያ ለሻደይ በዓል ጨዋታ አስፈላጊ ባሕላዊ አልባሳትን ከሞላ ጎደል እነኾ:-
👉 አልባሳት:- ቀሚስ፣ መቀነት፣ ጫማ፣ ሻሽ
👉የፀጉር ስሬት፡- ግልብጭ፣ አንድ እግራ፣ ግጫ፣ አልባሶ፣ ሳዱላ፣ ጋሜና ቁንጮ፣ ጐፈሬና፣ የእንጨት ማበጠሪያ
👉 ጌጣጌጦች:- ኩል፣ ድሪ፣ ድኮት፣ አልቦ፣ ዛጎል፣ ጠልሰም መስቀል፣ አምባር፣ ማርዳ፣ ድባ፣ አሸን ክታብ፣ ስቃጫ… የመሳሰሉትን በመልበስ እናቶች፣ ልጃረገዶች እና ሕፃናት የሻደይ በዓል ጨዋታን በድምቀት ያከብሩታል፡፡
የተዘጋጁ ያማሩ እና የተዋቡ ሴቶች አልፎ አልፎ በዙሪያቸው በታጀቡ ጎረምሳዎች ይጠበቃሉ፡፡ እንደ መታደል ኾኖ አካባቢያችን ተፈጥሮ በለገሰችው የሻደይ ቅጠል ወገባቸው ላይ አስረው ቃና መልካም ጣዕመ ዜማዎችን በመላበስ ቅድሚያ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ይገሰግሱና አበባ በመጣል የደንቡን ያደርሳሉ፡፡
ከዚያም ወደ እያንዳንዱ ሰው የመኖሪያ ቤት በመትመም እያዜሙ “አስገባኝ በረኛ አስገባኝ ከልካይ እመቤቴን ላይ” በማለት በሻደይ ጨዋታ ዙሪያ ከ16 በላይ ጣዕመ ዜማዎችን እያፈራረቁ ይዘፍናሉ፣ ይሸለማሉ፣ ይመረቃሉ፡፡ ባሕላዊ አሴቶችንም ከልማት ጋር በማስተሳሰር የቱሪስት መስህብ ይኾኑ ዘንድ የገቢ ምንጭ መፍጠር እየቻልን በመረጃ እጦት ተዳፍነውና ተሰውረው የሚገኙ ትኩረት ያልተሰጣቸው እና ያልተዳሰሱ በርካታ ሃብቶች እንዳሉንም ጥርጥር የለውም፡፡
ሻደይ ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ መምጣቱን መረጃውን በሰጡን የሃይማኖት አባቶች እና እናቶች መሠረት አስካሁን ድረስ ባሕላችን በድምቀት እያከብርን መጥተናል፤ ሌሎች ደማቅ እና ማራኪ ባሕላዊ ጨዋታዎችን እና ሰው ሠራሽ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንም ጭምር በመረጃ ተደግፈው ሊያዙ ይገባል፡፡
መረጃ የተዘጋንና የተደበቀን ግዙፍ ነገር መክፈቻ የሰረገላ ቁልፍ መኾኑን በመገንዘብ ሃብቶቻችን ሊባክኑ ወይም ደብዛቸው ሊጠፋ አይገባም፡፡ ወንዝ አይፈሬው የሻደይ ቅጠልም ከብዝኅ ሕይዎት አንዱ በመኾኑ ዕፅዋቱ ሊስፋፋ እና ሕልውናው ሊከበር ይገባል እንላለን፡፡
መረጃውን ያገኘነው ከዋግ ኽምራ ኮሙዩኒኬሽን ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!