በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተጠረጠረም ኾነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለ የጤና ሚኒስተር ገለጸ::

30

አዲስ አበባ: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በአጠቃላይ ዝግጁነት እና ቅኝት ሥራዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል:: የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) በሽታ በዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችል በሽታ ነው። ይህ በሽታ ከሰዉ ወደ ሰዉ እንዲሁም ከእንስሳት ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ ሲሆን የጥንቃቄ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ በፍጥነት ሊዛመት እንደሚችል ተጠቁሟል:፡

የበሽታው ምልክቶችም ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የጡንቻ እና የጀርባ ሕመም፣ ሽፍታ፣ የቆዳ ቁስለት እንዲሁም የአቅም ማጣት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ አሁን ላይ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ስርጭቱ በመስፋፋቱ እና የተቀናጀ የዓለም ዓቀፍ ምላሽ በማስፈለጉ የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች (PHEIC) መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕዝብ ጤና አሳሳቢ የኾነ ድንገተኛ አደጋ መኾኑን እንዲወሰን አድርጓል፡፡

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) በሽታ የአሕጉራዊ እና ኅብረተሰብ ጤና ስጋት መኾኑን አውጇል። በአሕጉራችን አፍሪካ ይህ ወረርሽኝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2024 ድረስ በ13 የአፍሪካ ሀገራት በአጠቃላይ 18 ሺህ ታማሚዎች እና 524 ሞት ሪፖርት መደረጉን እና መረጋገጡን የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ማሳወቁን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሽታው የስርጭት አድማሱን በማስፋት ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እየተስፋፋ በመኾኑ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል በሽታው አህጉራዊ የኅብረተሰብ ጤና ስጋት መኾኑን በይፋ አስታውቋል። የጤና ሚኒስቴርም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን የቅኝት እና የምላሽ እንዲሁም የድንበር አካባቢ ጤና ልየታ እና አገልግሎት ሥራዎችን የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማሥተባበሪያ እና ምላሽ ማዕከል በማቋቋም እየሠራ ይገኛል::

በተለይም ደግሞ በኬንያ አዋሳኝ ሦስት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ የመዉጫና መግቢያ ኬላዎች እንዲሁም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ላይ ከወትሮው በተጠናከረ ሁኔታ የቅኝት እና የልየታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የበሽታውን ምልክት የሚያሳዩ ሰዎችን ለይቶ ለማቆየትና ለማከም የሚያስችል ጊዜያዊ የሕክምና ተቋማት ለማዘጋጀት በየደረጃው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ሲሆን ምልክት የሚታይባቸው ተጠርጣሪዎች ከተገኙ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም ማሳወቅ ወይም ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ መኾኑም ተጠቁሟል;:
እስካሁን ድረስ ግን በኢትዮጽያ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተጠረጠረም ኾነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል::

ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዊንዶውስ 11 ዝማኔ
Next articleሻደይ መቼ እና እንዴት ተጀመረ?