የዊንዶውስ 11 ዝማኔ

43

ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኦፐሬቴንግ ሲስተም (OS) የኮምፒዩተርን ሀርድዌር እና ሶፍትዌሮችን የሚያሥተዳድርልን ሲኾን በስፋት የምናውቃቸው ዓይነቶች ደግሞ አንድሮይድ፣ ዊንዶውስ፣ ማክ እና ሊኑክስ ናቸው፡፡ ዊንዶውስ በማይክሮሶፍት ኩባንያ ተመርቶ የሚቀርብ ሲሆን በዓለማችን አብዛኞቹ ኮምፒውተሮች ላይ ተጭኖ አገልግሎትን እየሰጠ ያለ የኦፐሬቲንግ ሲስተም ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1985 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የማይክሮሶፍቱ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከ50 በላይ የዝማኔ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ ዊንዶውስ 11 በ2021 ይፋ ከተደረገ በኋለ እንኳን ሦስት ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ ዝማኔዎች የሚደረጉት ይፋ ከተደረጉት የኦፕሬቲንግ ሲስተም አገልግሎቶች ላይ ማስተካከያ እና አዲስ የሚጨመሩ ነገሮች ሲኖሩ ነው፡፡

አንድ ዝማኔ የተደረገለት የኦፕሬቴንግ ሲስተም ሲተዋወቅ ከዚህ በፊት የነበረው የቆይታ ዘመኑን ጨረሰ ይባላል፡፡ ይህ ሲባል ግን ነባሩ አይሠራም ማለት ሳይኾን የደኅንነት እና መሰል ድጋፎችን ማግኘት አይችልም ማለት ነው፡፡ በ2022 የተለቀቀው 22 ኤች 2 የተባለው የዊንዶውስ ስሪት በጥቅምት 2024 የቆይታ ጊዜውን እንደሚያጠናቅቅ ማይክሮሶፍት ኩባንያ አሳውቋል፡፡ በመኾኑም ዝማኔውን ለውጥ ወደ ተደረገለት ሥሪት መቀየር ያስፈልጋል፡፡

የሥሪት ዝማኔ (version update) ሲኖር የምናገኘው ጥቅም ጠንካራ የደኅንነት አገልግሎትን፣ ኮምፒውተሮቻችንን ለአጠቃቀም ምቹ እንዲኾኑ እና አዳዲስ ከመጡ መሣሪያዎች ጋር እንዲናበቡ ለማድረግ ያስችላሉ፡፡ የሚጨመሩ የደኅንነት ዝማኔዎች ቫይረሶችን እና ለሳይበር ጥቃት የሚያጋልጡ ፕሮግራሞች በኮምፒውተሮቻችን ላይ ችግር አንዳያደርሱ በመጠበቅ የኮምፒውተሮቻችንን አቅም በጤናማ ሁኔታ እንዲቀጥል ይረዳል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ላይ የሚደርሰውን ሥርቆት በመከላከል ረገድ ኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) የተጠረጠረም ኾነ የተረጋገጠ ታማሚ እንደሌለ የጤና ሚኒስተር ገለጸ::